የቡና ቅምሻና ባሬስታ ማሰልጠኛ ማዕከል ሊቋቋም ነው

119
አዲስ አበባ ግንቦት 6/2010 የቡና ቅምሻና ባሬስታ ማሰልጠኛ ማዕከል ሊያቋቁም መሆኑን የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን አስታወቀ። ማዕከሉ ለወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ፣ ለውጭ ግብይት ጥራትና ከጤና አኳያ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለስልጣኑ ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት/ዩኒዶ/ ጋር በመተባበር 'የቡና ቅምሻና ባሬስታ ማሰልጠኛ ማዕከል' ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ይገኛል። ማዕከሉ ባለሙያዎችን በማሰልጠን በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ለማቅረብ ያለመ ነው ብለዋል። ቡና ቆይዎች፣ ላኪዎችና አቅራቢዎች የሚፈልጉትን የሰለጠነ ባለሙያ እንዲያገኙ እንደሚያስችል ገልጸው፤ ይህም ወደ ውጭ የሚላክ የቡና ምርት ጥራት እንዲኖረው እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል። "ወጣቶችና ሴቶች ቡና መቁላት፣ መቅመስና ማፍላት ሰልጥነው በባለሀብቶች  ይቀጠራሉ" የሚሉት አቶ ሳኒ፤ በስራ ዕድል ፈጠራ ረገድም ሚናው የጎላ እንደሚሆን አብራርተዋል። "በአገር ውስጥ የምንጠቀመው ቡና በልማድ ላይ ተመስርቶ የሚፈላ ነው" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከጤና አኳያም መሻሻል እንዲፈጠር ያስችላል ነው ያሉት። ስለሆነም "የምንጠቀመው ቡና 'የጤና ችግር ይኖረዋል አይኖረውም፣ ምን ይቀላቀልበት፤ አይቀላቀልበት' የሚለውን  በሙያ ላይ ተመስርተው እንዲሰሩ ያደርጋል" ብለዋል። ማዕከሉን ለማቋቋም ቢሮ የማደራጀትና የስልጠና ግብዓት ማሟላት ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በመጪው ዓመት መጀመሪያ ወደ ስራ ለመግባት ታቅዷል ነው ያሉት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም