ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ "ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ" የሞባይል መተግበሪያን አሻሽሎ አቀረበ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት "ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ" የተሰኘው የስልጠና መስጫ የሞባይል መተግበሪያ ተሻሽሎ በአዲስ መልክ መቅረቡን አስታውቋል።

በሞባይል መተግበሪያው ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ተሰጥቷል።

"ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ" ዓለም አቀፉን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቁልፍ ሚና ያላቸውን የጤና ባለሙያዎች አቅም ለማጎልበት በጤና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በግንቦት 2012 ዓ.ም ስራ ላይ የዋለ የሞባይል መተግበሪያ ነው።

መተግበሪያው በኮቪድ ላይ ከተካሄዱ ጥናቶችና በኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚተገበሩ መመሪያዎች አንጻር ተሻሽሎ በአዲስ መልክ መቅረቡ ተገልጿል።

በዚህም የኮቪድ-19 በሽታ ቅኝትና አሰሳ፣ ሕክምና፣ የላቦራቶሪ አገልግሎት፣ ብክለትን መከላከልና መቆጣጠር፣ የአደጋ ስጋት ተግባቦትና የኅብረተሰቡን ተሳትፎ የተመለከቱ የስልጠና ርዕሰ ጉዳዮች በመተግበሪያው ተካተዋል።

የቤት ውስጥ ልየታና እንክብካቤ፣ በትምህርት ቤት ወረርሽኙን የመከላከልና የመቆጣጠር እርምጃዎችም በመተግበሪያው የስልጠና ርዕሶች መሆናቸው ተገልጿል።

በሞባይል መተግበሪያው የሚሰጠውን ስልጠና ለማገዝ የማስተማሪያ ቪዲዮዎች፣ የምዘና ጥያቄዎች፣ ግብረ መልሶች እንዲሁም ጥያቄዎች መካተታቸውም በመግለጫው ተመላክቷል።

መተግበሪያውን በመጠቀም የሚሰጠውን ስልጠና በአግባቡ ተከታትለው ለሚጨርሱ ሰልጣኞች የምስክር ወረቀት መዘጋጀቱም ነው የተጠቀሰው።

ባለፈው ዓመት ብቻ መተግበሪያውን ካወረዱ ከ10 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የጤና ባለሙያዎች እንደሆኑም ተገልጿል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮቪድ-19 ምላሽ ዋና አስተባባሪ አቶ አስቻለው አባይነህ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ያለውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የጤና ባለሙያዎችን በእውቀትና በክህሎት ማብቃት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በመተግበሪያው የሚሰጠውን ስልጠናም ባለሙያዎቹ ባመቻቸው ጊዜና ቦታ የሚሰጥ መሆኑ ሰፊ የሰው ሀይል በማብቃት ምላሽ የመስጠቱን ስራ በተጠናከረ መልኩ ማከናወን ያስችላል ብለዋል።

የሞባይል መተግበሪያው የሚሻሻሉ መመሪያዎችና አሰራሮች ሲኖሩም ባለሙያው ወቅታዊ መረጃ እንዲኖረው በማድረግ ለተቀናጀ ስራና ውጤታማነት ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

አቶ አስቻለው የጤና ባለሙያዎች መተግበሪያውን በሞባይላቸው በመጫን የኮቪድ-19 ስልጠና እንዲወስዱና ኮቪድን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ ላይ እንዲሳተፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

መተግበሪያው በትምህርት ቤቶች የኮቪድ-19 መከላከል ስራን ያካተተ በመሆኑ መምህራንና ሌሎችም አካላት እንዲጠቀሙበትና ስልጠናውን እንዲወስዱም ጥሪ አቅርበዋል።

http://bit.ly/3apv5J2 የሚለውን ማስፈንጠሪያ በመጠቀም በሞባይል ስልክ እንዲሁም በታብሌት ላይ በመጫን ስልጠናውን በነጻ መከታተል እንደሚቻል አቶ አስቻለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም