ድሉ የአንድነት ምንጭ ሆኖ ለሃገር ግንባታ ለመጠቀም የበኩላቸውን እንደሚጥሩ ወጣቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ድሉ የአንድነት ምንጭ ሆኖ ለሃገር ግንባታ ለመጠቀም የበኩላቸውን እንደሚጥሩ ወጣቶች ገለጹ
ደብረ ማርቆስ፤ የካቲት 16/2013(ኢዜአ) የአድዋ የድል በዓል የጥንካሬና የአንድነት ምንጭ ሆኖ ለሃገር ግንባታ እንዲውል ለመጠቀም የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ የምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ማርቆስ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
125ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያን በዓል አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ወጣቶች በሰጡት አስተያየት ቅድመ አያቶቻቸው በአድዋ ድል ያበረከቱትን የነጻነት እና የአንድነት ቱርፋት አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል።
ከወጣቶቹ መካከል ዳንኤል ቢመልስ ''ጀግኖች አባቶቻቸን አንድ ሆነው በከፈሉት መስዋትነት የጎላ ዝና ያላት ሀገር እንድትኖረን አድርገዋል'' ብሏል።
በዚህም አሁን ያለው ትውልድ በነጻነት እንዲኮራ እድል እንደተፈጠረለት ተናግሯል።
"እኛ ወጣቶች የሀገራችን ስምና ዝና በማስጠበቅ ከፍታዋን ለማሳደግ ዘረኝነት በማስወገድ የአባቶቻችን ታሪክ እንደግማለን'' ብሏል።
ቅድመ አያቶች ሀገሪቱ ውጭ ወራሪ በሚተናኮላት ጊዜ ያደረጉት የአንድነት፣ የመተሳሰብ እና የመረዳዳት ተግባር አንድነት ሀይል መሆኑን አስተምሮናል ሲል የገለፀው ደግሞ ወጣት ለአለም ያዛቸው ነው።
የአሁኑ ትውልድ ዘረኝነት፣ ጥላቻ፣ እርስ በእርስ መጠራጠርና እራስ ወዳድነት በማስወገድ ከአድዋ ድል አድራጊ አባቶች ታሪክ መውረስ እንደሚጠበቅበት ተናግሯል።
እኔም በበኩሌ አንድነታችን የሚያጠናክሩ በርካታ ስራዎችን በበጎ ፈቃደኝነት እየተሳተፍኩ የራሴን ጥረት እያደረግሁ ነው ብሏል።
ወጣት የኔሁን ዋሌ በበኩሉ ቅድመት አባቶች ሀገርን አሳልፎ ላለመስጠት ድርና ማግ ሆነው አንድነታቸውን አስጠብቀው ማኖራቸውን አውስቷል።
ይህ ድል ዋጋ የሚኖረው ለዚህ ትውልድ ስንቅ ሆኖ ማገልገልና ሃገርን ከጥፋት መታደግ ሲቻል መሆኑን አመልክቷል።
እኛ ወጣቶች ደግሞ ዘመናዊነት የታከለበት ልእልናን በማጎልበት አንድነታችን አጠናክረን እኛነታችን ከሚሸረሽሩ እና የሀገራችን ሉአላዊነት ከሚጋፉ ማንኛውም ጉዳዮች መመከት ይገባል ብሏል።
ለዚህ ደግሞ ጁንታው ዘርቶት የነበረውን የጥላቻ መርዝ እና ቂም በማስወገድ ለጋራ እድገት አብሮ ለመስራት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጿል።
ዘንድሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የካቲት - የአድዋ ወር በሚል መሰየሙንና ይህም " በአድዋ የተፈጸመው ድል፤ በህብረብሄራዊ አንድነታችን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ ይደገማል" በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ነው።