መጪው ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
መጪው ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ
ዲላ ፤የካቲት 16/2013(ኢዜአ) መጪው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በጌዴኦ ዞን የሚቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ፎረም ምስረታ ውይይት በዲላ ከተማ ተካሄዷል።
በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ -ፍትህ ፓርቲ /ኢዜማ/ ጌዴኦ ዞን ተወካይ አቶ ደሳለኝ ደያሶ በዞኑ ለክልልና ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች የእጩ ምልመላ ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
መጪው ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እስከ ቀበሌ ለሚገኙ አባላት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየሰራን ነው ብለዋል።
በዞኑ ውይይት ለማድረግ የስብሰባ አዳራሽ ያለመፍቀድ ሁኔታ እንደሚስተዋልና ይህንንም በመነጋገር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና ርዕዮት አለም ዘርፍ የዞኑ ሃላፊ አቶ አካሉ ሃልቻዬ ናቸው።
በተለይ በዞን ደረጃ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅርበት በውይይት ለመፍታት በዞኑ የሚንቅሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ፎረም መቋቋሙ አጋዥ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ምርጫው ለሁሉም ተፎካካሪ ፖርቲዎች ፍትሃዊ እንዲሆን ብልጽግና ፓርቲ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንደሚወጣ ተናግረዋል።
የጌዴኦ ህዝብ ዴሞክራያዊ ድርጅት /ጌህዴድ/ የዞኑ ዋና ጸሃፊ አቶ ብርሃኑ ጎበና በበኩላቸው ምርጫው የተሻለ ሃሳብ ይዞ በመምጣት በሰላማዊ መንገድ የህዝቡን ድምጽ የሚያገኝ ፓርቲ አሸናፊ የሚሆንበት ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ድርጅታቸው ሀላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።
በመድረኩ የፎረሙ መተዳደሪያ ደንብና የቃልኪዳን ሰነድ ቀርቦ ተሳታፊዎቹ ከተወያዩበት በኋላ የጸደቀ ሲሆን የፎረሙ ዋናና ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም ጸሃፊ ተመርጠዋል።