የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን ስርዓተ ቀብር ነገ ይፈጸማል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን ስርዓተ ቀብር ነገ ይፈጸማል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2013(ኢዜአ ) እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን ስርዓተ ቀብር ነገ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ-ክርስቲያን ይፈጸማል።
የእርቀ ሠላም ኮሚሽን የሎሬቱን ህልፈት የሚዘክር መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ የሃይማኖት አባቶች፣ የእርቀ ሠላም ኮሚሽን አባላትና እንግዶች ተገኝተዋል።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን በተለያዩ መስኮች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ቀርቧል።
ካበረከቱት አስተዋኦ መካከል በአገሪቷ ሠላምና ወንድማማችነት እንዲጎለብት በእርቀ ሠላም በኩል ያበረከቱት አስተዋጽኦ ተወስቷል።
በላየንስ ክለብ ለረጅም ዓመታት የሰጡት አገልግሎት፣ በቀይ መስቀል ማህበርና በኢትዮጵያ ስካውት ማህበር አገር ወዳድ ወጣት እንዲፈራ በማድረግ ረገድ በርካታ ስራዎች መስራታቸውም ተወስቷል።
የእርቀ ሠላም ኮሚሽን ምክትል ሰብሳቢ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ እንደተናገረችው፤ ሎሬቱ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ኮሚሽኑ የያዛቸው ዓላማዎች እንዲሳኩ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በተለይም ኮሚሽኑ እንዲጠናከር ከአጋር አካላት ጋር ቅንጅት እንዲፈጠር ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን፤ በኮሚሽኑ አቅም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ በኩልም በሳል አመራር ሲሰጡ እንደነበር አንስታለች።
እንደ ሎሬት የትነበርሽ ገለጻ በተለያዩ አካባቢዎች እርቅ እንዲመጣ ከጠቅላይ ዐቃቢ ህግና ከሠላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ውጤታማ ስራዎች አከናውነዋል።
የዓለም ሎሬት ሕይወታቸው እስካለፈበት ድረስ ስራቸውን ሲሰሩ እንደነበር በማስታወስ "የእርሳቸው ዓላማ ከግብ እንዲደርስ እኛ የኮሚሽኑ አባላት ተግተን እንሰራለን" ብላለች።
የእርቀ ሠላም ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን በጤናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ አልፎ በምስራቅ አፍሪካ የሰጡት አገልግሎት ተጠቃሽ መሆኑን ገልፀዋል።
በአለርት የሕክምና ማዕከል የሥጋ ደዌ ሕክምና በመስጠት የነበራቸውን አስተዋጽኦም አንስተዋል።
የላየንስ ክለብ ተወካይ ዶክተር ሰለሞን ገሰሰ ሎሬቱ በክለቡ 40 ዓመታት ማገልገላቸውን የገለጹ ሲሆን በበርካታ የጤና ዘርፎች ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ተወካይ አቶ ክብረት ፀሐይ "የዓለም ሎሬት ጥበበ በሽግግሩ ወቅት 80 ሺህ ወታደሮች ከሱዳን እንዲመለሱ ያደረጉት አስተዋጽኦ ትልቅ ነበር" ብለዋል።
"በእኛ በኩል የሰብዓዊነት ዋርካ እንደወደቀ እንቆጥረዋለን" ያሉት ተወካዩ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጆቻቸውና ለኮሚሽኑ አባላት መጽናናትን ተመኝተዋል።
የስካውት ማኅበር ተወካይ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄ ባስተላለፉት መልዕክት በርካታ ወጣቶች አገር ወዳድነትና ዜግነት ላይ ያላቸው ምልከታ እንዲሰፋ ማስተማራቸውን ጠቅሰዋል።
"ሰው አገሩን ማገልገል ያለበት ለጥቅም ሳይሆን ለህሊናው መሆኑን ከእርሳቸው ሕይወት በላይ አስተማሪ የለም" ሲሉ አክለዋል።
በመርሃ ግብሩ የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበን ለመዘከር ጧፍ የማብራት ሥነ ስርዓት የተካሄደ ሲሆን በዝግጅቱ የተገኙ እንግዶች የሀዘን መግለጫ መዝገብ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን የቀብር ስነ ስርዓት ነገ በቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ከቀኑ በ8 ሠዓት ከ30 እንደሚፈጸም ታውቋል።