ቀጥታ፡

የአድዋን በዓል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለማክበር ዝግጅት ተደረገ

አሶሳ፤ የካቲት 15/2013 (ኢዜአ)125ኛውን የአድዋ ድል በዓል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደረጃ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ ወይዘሪት ምስኪያ አብደላ ለኢዜአ እንደገለጹት የድል በዓሉ በክልሉ የካቲት 17/2013 ዓ.ም. በድምቀት ይከበራል፡፡

ህብረተሰቡ በበዓሉ እንዲሳተፍ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ አምስት አብይ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ዝርዝር ተግባራትን በመንደፍ ዝግጅት አጠናቀዋል ብለዋል፡፡

"አባቶቻችን ወራሪውን ጣሊያን አሳፍረው የመለሱት በሃይማኖት፣ ዘር እና ቋንቋ ሳይከፋፈሉ ነው፤  ይህን ታሪክ ለተተኪው በማስተላለፍ ረገድ ሰፊ ስራ ይጠብቀናል" በማለት፤ የበዓሉ አከባበር ዓላማም ይህንን ለመስራት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

"አሁን ያለው ትውልድ የአባቶችን የዓድዋ ታሪክ እንየደገመ እንደሚገኝ ይሠማኛል" ያሉት ወይዘሪት ምስኪያ፤ "በራሳችን አቅም መልማት እንችላለን በሚል ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን የህዳሴ ግድብ ለዚህ አብነት ነው" ሲሉ አብራርተዋል፡፡

አድዋን ምሳሌ በማድረግ የበለጠ ከተባበርን ሌሎች በርካታ ግድቦችን መስራት እንችላለንም ነው ያሉት ሃላፊዋ፤ ይህን ለማሳካት ኢትዮጵያዊያን የህዳሴውን ግድብ እንደአይናቸው ብሌን በመጠበቅ የውስጥ እና የውጪ ተጽዕኖዎች በአንድነት መመከት አለባቸው ብለዋል።

በሀገር ደረጃ  የካቲት የአድዋ ወር በሚል ሲሰየም "በአድዋ የተፈጸመው ድል፤ በህብረብሄራዊ አንድነታችን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ ይደገማል"መሪ ሀሳብ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም