ምርጫው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ዜጎች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ምሁራን ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ዜጎች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ምሁራን ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15 /2013 (ኢዜአ) መጪው አገራዊ ምርጫ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን እያንዳንዱ ዜጋ የተጣለበትን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን አስገነዘቡ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮቪድ-19 መከላከል ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀ መሆኑ ይታወቃል።
የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር አቶ ኩሌ ኩርሻ ምርጫው በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለውን የሠላምና ጸጥታ ችግር ለመፍታት መፍትሔ እንደሚሆን ተናግረዋል።
"ችግሮችን በማውራት መፍትሔ አናመጣም፤ ማውራት የሚያስፈልገው ችግሮችን ተረድተን መውጫ መንገዶችን ማበጀት ነው" ብለዋል።
"ምርጫ ከችግር የመውጫ አንድ መንገድ ነው" ያሉት አቶ ኩሌ፤ መንግስትን ሕጋዊ ለማድረግና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለመፍታት ምርጫ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በመሆኑም 6ኛው አገራዊ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች በተለየ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የዜጎች ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ሌላዋ የሕግ ባለሙያ ወይዘሪት ቤተልሄም መታፈሪያ በበኩላቸው ዜጎች የሁሉንም ህይወት ሊቀይር የሚችል አማራጭ ይዞ የመጣን የፖለቲካ ፓርቲ በመለየት ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው መክረዋል።
ዜጎች በዜግነት የሚጠበቅባቸውን ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
በተለይም ከምርጫ ጋር የተያያዙ የተሳሳቱ ፕሮፓጋንዳዎችን ከመስራት፣ ተጨባጭ ያልሆኑ መረጃዎችን ከመልቀቅ፣ የሰውንም ስም ማጥፋትና ከተለያዩ ነገሮች መታቀብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ይህ ደግሞ ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ መጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።
የአመራርና ፖሊሲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አለማየሁ ደበበ "የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሕግ አክብረው ከመበሻሸቅ፣ ከመነታረክ፣ ከጥበት ነጻ ሆነው የተሻለች አገርን ሊያሳየን በሚችል መልኩ ፕሮግራማቸውን ማስተዋወቅ አለባቸው" ብለዋል።
ኢኮኖሚውን በሚመለከት፣ የአገሪቱን ማህበራዊ ገጽታ በመለወጥ ረገድ ምንድነው ያላቸው፣ የፖለቲካ ፕሮግራማቸው ምንድነው፣ መንግስት ከምርጫ ቦርድ ቀጥሎ ማቴሪያል በማቅረብ የሌሎች ተፎካካሪዎችን ሠላምና ጸጥታ የማስከበር ሌሎች ምርጫን ሊያደናቅፉ የሚችሉ መንገዶችን አስቀድሞ ለይቶ እልባት መስጠት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የአመራርና አስተዳደር የግል አማካሪ አቶ ሃብታሙ ለገሰ "ማኅበረሰቡም ስለ ምርጫ ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ሳይዛባ ወገንተኝነት በሌለበት ሁኔታ ማግኘት እንዲችል እያንዳንዱ የሚዲያ ተቋም መስራት አለበት" ብለዋል።