የክልል መንግስታትና የፖለቲካ ድርጅቶች በኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የክልል መንግስታትና የፖለቲካ ድርጅቶች በኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ
ባህርዳር አሶሳ ሐረር ሀምሌ 19/2010 የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስታት እንዲሁም የሐብሊ ማዕከላዊ ኮሚቴና በሐረሪ ክልል የኦህዴድ ጽህፈት ቤቶች በኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግስትየኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ማሳያ የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ እና በክልሉ ብሎም በሀገር ደረጃ ከፍተኛ አመራር በነበሩት አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ድርብ የሆነ ጥልቅ ሀዘን ለኢዜአ በላከው መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡ "ኢንጅነር ስመኘው በቀለ የጀመሩት ታላቁን ፕሮጀክት ሳያጠናቅቁ ማለፋቸው ታላቅ ሀገራዊ አደራን የጣሉብን መሆኑን በመገንዘብ የክልላችንን መንግስትና ህዝብ የህዳሴውን ግድብ ለማጠናቀቅ በእልህና በቁጭት ይተጋል" ብሏል፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግስት ለኢንጅነር ስመኘው በቀለ እና ለአቶ ተስፋዬ ጌታቸው ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች መፅናናትን ተመኝቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ በላከው የሀዘን መግለጫ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ፍላጎት በሆነው በአባይ ወንዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር የግድቡን ግንባታ በብቃት መምራት የቻሉ ቁርጠኛ አመራር እንደነበሩ አስታውቋል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚከናወነው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ውስጥ እንደመሆኑ ኢንጅነሩ ከክልሉ መንግስትና ግድቡ ከሚገነባበት አካባቢ ማህበረሰብ ጋር ጥብቅ ቤተሰባዊ ግንኙነት እንደነበራቸው በማስታወስ ለክልሉ ህዝቦች ሃዘኑ የከበደ መሆኑን ገልጿል፡፡ ሃዘኑ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑም ለመላው የሀገሪቱ ህዝብ ጨምሮ ለኢንጅነሩ ቤተሰቦች፣ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል፡፡ በሌላ በኩልም የሀረሪ ብሄራዊ ሊግ/ሐብሊ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የክልሉ ኢህዴድ በኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል፡፡ ድርጅቶቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ግድቡ ዕውን እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት የመንግስትና የህዝብ ኃላፊነትና አደራ ለመወጣት በከፍተኛ ቁርጠኝነት አገልግለዋል። ግድቡም አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ መስዕዋትነት ከፍለዋል። ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ከዚህ አለም በሞት ቢለዩም የእሳቸው አሻራ ያረፈበትን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር ለማድረስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል። ድርጅቶቹ በታታሪ የፅናትና የቁርጠኝነት ተምሳሌቱ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጰያ ህዝብ መፅናናትን ተመኝተዋል።