የኤርትራን ወታደራዊ መለዮ ለብሰው የህዝቡን ንብረት የሚዘርፉና ሴቶችን የሚደፍሩት ጁንታው የፈጠራቸው ወንበዴዎች ናቸው...የሰሜን ትግራይ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ

70

የካቲት 15/2013 ( ኢዜአ) በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ስለ ትግራይ ክልል የሚሰራጨው መረጃ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በትክክል እንደማያሳይ የሰሜን ትግራይ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ገለጹ።

የሰሜን ትግራይ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሙሉብርሃን ኃይሉ የኤርትራን ወታደራዊ መለዮ ለብሰው የህዝቡን ንብረት የሚዘርፉትና ሴቶችን የሚደፍሩት የጁንታው ስርዓት የፈጠራቸው ወንበዴዎች እንጂ የኤርትራ ወታደሮች አይደሉም ብለዋል።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሰሜን ትግራይ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሙሉብርሃን ኃይሉ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን በእብሪተኝነት በለኮሰው እሳት ራሱም ተለብልቦ ለበርካታ ዜጎች ሞትና ለንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ በውጭ አገር ያሉና በእግራቸው ጫካ ለጫካ የሚኳትኑ ቀሪ የጁንታው አባላት በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት የትግራይን ህዝብ ለማታለል እየሞከሩ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳለ የገለጹት አቶ ሙሉብርሃን የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በአካል ተገኝቶ መዘገብ የሚፈልግ የመገናኛ ብዙሃን ካለ በሩ ክፍት ነው በርቀት ሆኖ የሀሰት መረጃ ማሰራጨት ግን ተገቢ አይደለም በማለት ተናግረዋል።

ህወሓት ባለፉት 46 ዓመታት የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጵያዊነት ለመነጠል የሀሰት ትርክት እየደረሰ ከማወናበድ ውጭ ምንም ጥቅም እንዳላስገኘለት ህዝቡ ተገንዝቧል ብለዋል አቶ ሙሉብርሃን።

አክሱማዊያን ኢትዮጵያዊያን አልነበሩም የሚል የሀሰት ድርሰት ተዘጋጅቶ የትግራይን ኢትዮጵያ ለመነጠል የሞከረ የራስ ወዳዶች ስብስብ ነው በማለትም ገልጸዋል።

የትግራይ ህዝብም ህወሃት የራሱን አጀንዳ ብቻ የሚያስፈጽም የማፍያ ስብስብ መሆኑን በመረዳት የመከላከያ ሰራዊቱ የተጠናከረ ህግ የማስከበር እርምጃ እንዲወስድ መረጃ በመስጠትና አቅጣጫ በመጠቆም እየተባበረ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ ሙሉብርሃን እንደሚሉት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል ሀብት እየዘረፉ ነው ሴቶችን እየደፈሩ ነው በሚል የሚሰራጨው የተሳሳተ መረጃ መሬት ላይ ያለውን ሀቅ አያሳይም።

የጁንታው ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ካደረሰ በኋላ አጸፋውን መቋቋም ሲሳነው በስርቆትና በተለያዩ ወንጀሎች ማረሚያ ቤት የነበሩ ወጣቶችን በመልቀቅ ለዘረፋ አሰማርቷቸዋል ብለዋል።

ይህ ብቻ አይደለም ስርዓቱ በዘመኑ የፈጠራቸውን ስራ አጥ ወጣቶች መሳሪያ በማስታጠቅና የኤርትራን ወታደራዊ መለዮ በማልበስ ሴቶችን እንዲደፍሩ በማድረግ የኤርትራ ወታደሮች ናቸው እንዲባል ጥረት አድርጓል ይላሉ።

የኤርትራ ወታደሮች ህወሓት ባሰማራቸው ዘራፊዎች ወደ ኤርትራ ድንበር ሄዶ የነበረ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ለትግራይ ህዝብ አስረከቡ እንጂ የትግራይን ህዝብ ንብረት አልዘረፉም የሚሉት አቶ ሙሉብርሃን ይህ በህዝቡ መካከል ልዩነት ለመፍጠር የተደረገ የህወሃት የተለመድ ሴራ ነው ብለውታል።

የህወሃት ቡድን የትግራይን ህዝብ ከሁሉም ጋር በማጋጨት ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ ለማድረግ ያደረገውን የ46 ዓመታት ስብከት ለማጥፋት ከአማራና ከኤርትራ ህዝብ ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ውይይት ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።

በትግራይ ክልል የሚቀርበው ሰብዓዊ እርዳታ በቂ ነው ባይባልም በአሁኑ ወቅት በረሃብ ምክንያት የሚሞት ሰው እንደሌለ ገልጸዋል።

አቶ ሙሉብርሃን እንደሚሉት የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ገመድ በሌሊት መቁረጥ ወይም አንድን ሰው በድንገት መግደል ህወሃት ዛሬም በትግራይ ምድር የፈለገውን ማድረግ ይችላል ማለት አይደለም።

ህወሃት በትግራይ ክልል ጥቃት መፈጸም ቀርቶ ራሱን መከላከል በማይችልበት ሁኔታ ጫካ ለጫካ ራሱን ለማዳን የሚኳትን ከዜሮ በታች ያለ ሆኗል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም