የአድዋ ድልና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚና 'ከሱባዔ እወጃ እስከ ዘመቻ' - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድልና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚና 'ከሱባዔ እወጃ እስከ ዘመቻ'
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15 /2013 (ኢዜአ) የአድዋ ድልና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚና 'ከሱባዔ እወጃ እስከ ዘመቻ' የዘለቀ ነበር።
የቅኔ፣ የአቋቋምና የትርጓሜ መጽሃፍት ሊቁ፤ ሊቀ-ጠበብት ሣህለማርያም ተፈራ የአድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን ባህሪያት መገለጫ ታላቅ ድል ስለመሆኑ ያነሳሉ።
በአድዋ ድል ስኬት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነበራት ተጋድሎ ከፍተኛ መሆኑን ሲያስታውሱም 'ከፀሎት እስከ ዘመቻው ቦታ የዘለቀ ነው' ይላሉ።
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ለዘመቻው ክተት ሲያውጁ በ'ማርያም' መማላቸው፤ የእምነቱ ተከታዮች እንዲዘምቱ ልዩ ንቅናቄ ማድረጉን ያወሳሉ።
በአድዋ ዘመቻ ከየግዛቱ ካህናት ጽላት ይዘው በመንገድ ላይ ሌሊት ሠዓታት እየቆሙ፣ ማለዳም ኪዳን እያደረሱ ስለመዝመታቸውም እንዲሁ።
በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያኗ የኢትዮጵያው ንጉሥ ጦር ድል እስኪቀዳጅ ድረስ ዘመቻ ያልሄደው ምዕመን በጸሎትና ምህላ እንዲቆይ ሱባዔ አውጃ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ጸሎት ምህላዋም ሰምሮ ድሉ ለኢትዮጵያ እንዲሆን ማስቻሉን "የንጉሱ የጦርነት ድል እስከሚሰማ ድረስ በየትኛውም ቤተክርስቲያን ሱባዔ እንዲያዝ ያወጀች ቤተክርስቲያን ናት" ሲሉ ገልጸዋል።
ቤተ-ክርስቲያኗ የአድዋን ታሪክ በመናገሻ ገነተ-ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም ብቻ እንደምትዘክረው የገለጹት ሊቀ ጠበብቱ፤ በአድዋ መስዋዕት የሆኑ አባቶችና እናቶች መታሰብ እንዳለባቸው ያምናሉ።
በአድዋ፣ በመቀሌና በአምባላጄ ጦር ሜዳዎች የተሰዉ ኢትዮጵያዊያንን ታሪክ በግዕዝና በአማርኛ ስንክሳር በመጻፍ በየዓመቱ እንዲዘከሩ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
"ይህ ደግሞ የባለታሪኮችን ዝርዝር በቤተ መዘክር በማስቀመጥ ጎብኚዎችም እንዲመለከቷቸው ያስችላል" ብለዋል።