ቀጥታ፡

የተለያዩ የመንግስት ተቋማት በኢንጅነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ

አዲስ አበባ ሐምሌ 19/2010 የተለያዩ የመንግስት ተቋማት በኢንጂኒር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ ኤጀንሲና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላኩት መግለጫ በኢንጂኒር ስመኘው ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ የአገሪቱን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በአንድ የጋራ ዓላማ ተሰልፈው ክንዳቸውን በልማት እንዲያነሱ ታላቅ ተግባር የፈፀሙ ናቸው። ኢትዮጵያውያን እኚሀን ታላቅ ሰው በሞት ቢያጧቸውም በህዳሴው ግድብ ምክንያት በታሪክ ሲዘከሩ አንደሚኖሩም ተቋማቱ ገልፀዋል። ለቤተሰቦቻቸው፣ ለስራ ባልደረቦቻቸው እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትንም ተመኝተዋል። የኢንጂኒር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈት ሁሉንም ቢያስደነግጥም መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በበለጠ ህዝባዊ አንድነትና በጋለ ሀገራዊ ወኔ የህዳሴውን ግድብ በማጠናቀቅ የቆሙለትን ዓላማ እናሳካለን ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም