ቀጥታ፡

የአድዋ ጦርነት ሴቶች በአመራር ሰጪነት ጭምር የተሳተፉበት ነው - የታሪክ ምሁራን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15/2013 ( ኢዜአ) የአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ስንቅ በማቀበል ጦሩ እንዲፀና ከማድረግ ባሻገር በአመራርነት የተሳተፉበት እንደሆነ የታሪክ ምሁራን ይገልፃሉ።

ምሁራኑ ሴቶች በታሪክ የነበራቸውን ጉልህ ሚና በአሁኑ ትውልድም በተለያዩ ኃላፊነቶች የአመራር ብቃታቸውን በማሳየት እየደገሙት እንደሆነ ለኢዜአ ገልፀዋል።

የዛሬ 125 ዓመት ጥቁር ሕዝቦች በነጮች ላይ ድል የተቀዳጁበትና ኢትዮጵያም የጣሊያን ጦር ድል በመንሳት ነጻነቷን ያወጀችበትን የአድዋ ድል ታሪክ ሰንዶታል።

ሴቶች ለአድዋ ጦርነት ከአገሪቷ የተለያዩ አቅጣጫዎች የተሰባሰበውን ጦር በስንቅ ከመደገፍ ባሻገር ጦር እስከመምራት የደረሰ ሚና እንደነበራቸውም የታሪክ መጻህፍት ያስረዳሉ።

ደራሲው ታደለ ገድሌ "የነገሥታት ገድሎችና የፍቅር ታሪኮች" በሚል መጽሀፉ እቴጌ ጣይቱን ጠንካራ አስተሳሰብና ብሩህ አዕምሮ የነበራቸው፤ እስከ ንግሥናቸው ፍፃሜም የአፄ ምኒልክ የቅርብ ረዳት ሆነው አገራቸውን ማገልገላቸውን ይገልጻል።

በመጽሀፉ እንደተመለከተው እቴጌ ጣይቱ የጣሊያን ሁኔታ እያሰጋ ሲመጣ የጦርነቱ ደጋፊና መሪ ተዋናይም ነበሩ።

በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ላይ ለመምከር ሚኒስትሮች፣ የጦር አለቆችና መኳንንት በተጠሩበት ጉባኤ እቴጌ ጣይቱ የሕዝቡን ወኔ የሚቀሰቅስ ንግግር ማድረጋቸውን ይኸው መጽሀፍ ያትታል።

እቴጌይቱ "እኔ ሴት ነኝ፤ ጦርነት አልወድም ሆኖም ኢትዮጵያን የጣልያን ጥገኛ የሚያደርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ። መልኩ ከመልካችን የማይመሳሰል፤ ቋንቋው ከቋንቋችን የማይገጥም፤ ፈጣሪ በባህር ከልሎ የሰጠን አገራችንን የሚቀማ ጠላት መጥቶ እንዴት ዝም እንላለን? እንዋጋለን እንጂ" ነበር ያሉት።

የጦርነቱ መሰናዶ ሲደረግ በእቴጌ ጣይቱ አዝማችነት የሚመራ 3 ሺህ ሠራዊት እና 6 ሺህ ፈረሰኛ ለአድዋ ጦርነት ማሰለፋቸውንም ደራሲ ታደለ በመፅሃፉ ጠቅሷል።

የመቀሌ የጠላት ምሽግ በወንዶች ጀግንነት አልፈታ ሲል በሴት ብልሃት ለመጠቀም ንግስቲቱ እቴጌ ጣይቱ አዛዥ ዛማኔልን "አንተ ሂድና ውሃውን ለመያዝ ይመች እንደሆነ ስፍራውን ሰልለው፤ ሊቀመኳስ አባተንም አማክረው" ሲሉ አዘዙ።

ሊቀመኳስ አባተም "ስፍራው ጎድጓዳ ነው፤ ለጣሊያኖችም ቅርባቸው ነው፣ የውሃውና የምሽጉ ርቀት 150 ክንድ ይሆናል ነገር ግን እኔ በመድፍ በሩን እጠብቀዋለሁ። ዘበኛውም ለዓይን ሲይዝ ገብቶ ከወንዙ ይተኛል"  ብሎ ላከ እቴጌም ይህንኑ ለንጉሠ ነገሥቱ አለመለከቱ፤ ዓፄ ምኒልክም እሺ አሏቸው" ይላል መፅሀፉ።

እቴጌ ጣይቱ ባፈለቁት ዘዴ በሰው ኃይልና በመሳሪያ ብዛት በቀላሉ ሊፈታ የማይችለው የኢጣሊያ ጦር የመቀሌ ምሽግ ብትንትኑ ሊወጣ መቻሉም በታሪክ ሰፍሯል።

ይህ ኩነት ሴቶች በአድዋ ጦርነት ስንቅ ከማቀበልና ጦሩን ከማበርታት ባሻገር በወኔ ሲያዋጉና ስትራቴጂ ነድፈው ድል ሲያስመዘግቡ እንደነበር ማሳያ ነው ይላሉ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የታሪክ ምሁር ዶክተር አህመድ ሀሰን እንደሚሉት ከአድዋ ጦርነት በፊትም ጦርነት የሚመሩ ብርቱ ሴቶች ነበሩ።

የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ደግሞ አድዋ ለተጨቆነ ሕዝብ ህያው ተምሳሌት የሆነና ለድሉም የአገሪቷ ሕዝብ ሁሉ የድርሻውን አስተዋጽኦ ያደረገበት መሆኑን ነው ያነሱት።

እንደ አሁኑ ቀለብ በፋብሪካ ተቀናብሮ ለወታደሩ በማይላክበት በዚያ ዘመን ሴቶች ጉልበታቸውን ሰውተው በጦርነቱ የተሳተፉ መቶ ሺህዎችን ለመመገብ ስንቅ አዘጋጅተዋል ይላሉ።  

ይሁንና በአድዋ ድል የመልክዓ ምድር፣ የመጓጓዣ አውታሮች እንዲሁም የሴቶችን አስተዋፅኦ በተመለከተ በሚገባ ትኩረት አልተሰጠም ባይ ናቸው ፕሮፌሰር አህመድ።

"ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ሚናቸው በማጀትና በቤት የተወሰነ አይደለም በፖለቲካ መስክም የመሪነት ሚናን ሲወጡ ቆይተዋል" ያሉት ደግሞ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተርና የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ናቸው።

በአድዋ ጦርነት ሴቶች የነበራቸው ሚና ስንቅ ከማቀበል እስከ ጦርነቱን መምራት ድረስ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ምሁራኑ በአድዋ ጦርነት ጣሊያንን ድል ለማድረግ የነበረው የመተባበር መንፈስ ፆታ፣ ብሄርንና ሃይማኖትን የተሻገረ በመሆኑ በጋራ ውጤት ሊመዘገብ እንደቻለም አውስተዋል።

የሴቶች ተሳትፎና ውጤታማነት በአድዋ ያልተገደበ፣ ዘመን ተሻገሪ እንዲሁም በሁሉም ዘርፍ በጉልህ የተንጸባረቀ መሆኑንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም