ቀጥታ፡

የአድዋ ድል የመከባበር፣ የአብሮነትና የአንድነት ውጤት ነው -- በሰሜን ሸዋ የሀይማኖት አባቶች

የካቲት 15/2013(ኢዜአ) የአብሮነትና የአንድነት ውጤት ከሆነው የአድዋ ድል በመማር የሀገርን ክብር ማጠበቅ እንደሚገባ በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች አስገነዘቡ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሰላሌ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን  ሸፈራው ታደሰ  ለኢዜአ እንደገለጹት የህዝቦች የረጅም ጊዜ የመከባበርና  የአብሮ እሴት  ዘመናዊ ጦር የታጠቀውን የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ድል በማድረግ በአድዋ ድል መሰረት ጥሏል ።

ይህ የሕዝቦች ተከባብሮ በአንድነት የመኖር  ልማድ የአሁኗን  ኢትዮጵያ  እንዳቆየም  አመልክተዋል፡፡

"የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለቅኝ ገዢዎች አንገታቸውን ሳይደፉ በነፃነትና በእኩልነት እንዲኖሩ እድል የሰጠ ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንገላዉያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት የሰላሌ አጥቢያ አስተባባሪ ፓስተር ሰለሞን አየለ ናቸው ፡፡

የአሁኑ ትውልድ የአንድነት፣ የመከባበርና የመቻቻል ውጤት ከሆነው የአድዋ ድል በመማር የሀገሩን ክብር ማስጠበቅ እንደሚገባው አስገንዝበዋል ።

የኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የእስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሼኽ አብዱልሰመድ አብድራዛቅ የጥንት አባትና እናቶች  መስዋእትነት ከፍለው አድዋ ላይ  ድል  በመጎናጸፋቸው ሉአላዊት ሀገር ለማቆየት መቻላቸውን ተናግረዋል ።

በአሁኑ ወቅት የራሳቸው ድብቅ አጀንዳ ያላቸው ወገኖች በዘር፣ በሀይማኖትና በቋንቋ ሕዝብን ለመከፋፈል የሚያደርጉት ሙከራ የአድዋን ድል መሰረት ካለማወቅ የመነጨ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትን እንደ እምነቱ የያዘ ነው" ያሉት ሼኽ አብዱልሰመድ ትውልዱ የሀገሩን አንድነት ጠብቆ ለማቆየት ታሪክና ባህላዊ እሴቶችን ዞር ብሎ ማየት እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

የአድዋ ድል ለዘመናት የቆየው ተባብሮ ጠላትን የመመከት ውጤት መሆኑን በማመልከት፡፡

የአካባቢው የሀገር ሽማግሌና የህግ ባለሙያ አቶ ማሞ በላቸው "እንደ አድዋ ድል የመሰሉ የነፃነት፣ የእኩልነትና የፍትህ ድሎችን በዚህ ወቅት ለማስመዝገብ ሕዝቡ የቆየ ባህሉን መጠበቅ ይገባዋል" ብለዋል፡፡

ሀገርና ሕዝብን ከግል የፖለቲካም ሆነ የጥቅም ፍላጐት ነጥሎ በማየት የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

ሕዝቡ መብቱንና ነፃነቱን ለማስጠበቅ ከአድዋ ድል ብዙ ሊማር እንደሚገባ ጠቁመው ባህላዊ እሴቶች በአግባቡ ከተያዙ በልማትም ሆነ ወረራን በመመከት ጥሩ መሣሪያ እንደሚሆኑ አስረድተዋል ፡፡

ሀገራችን ቀድማ የደረሰችበት የጥንት ስልጣኔና የአድዋ ድልን ጠብቆ የማቆየት አደራ የተጣለው በአሁኑ ትውልድ ላይ መሆኑንም ባለሙያው አስገንዝበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም