የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን አጠናክረን ከተንቀሳቀስን የሚገዳደረን ሃይል እንደሌለ ማሳያ ነው..አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን አጠናክረን ከተንቀሳቀስን የሚገዳደረን ሃይል እንደሌለ ማሳያ ነው..አቶ ደስታ ሌዳሞ
ሐዋሳ የካቲት 14/2013 (ኢዜአ) የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን አጠናክረን መንቀሳቀስ ከቻልን የሚገዳደረን ሃይል እንደሌለ ማሳያ ነው ሲሉ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።
በሲዳማ ክልል የዘንድሮው 125ኛው የአድዋ ድል በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ በሐዋሳ ከተማ በደማቅ ሥነ ስርዓት ተከብሯል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት የአድዋ ድል የነጭ ወራሪ ኃይል በገሃድ የተሸነፈበት ታላቅ ታሪካዊ ክሰተት ነው።
"የሀገራችን ህዝቦች የሀገራቸውን ሉአላዊነት ለአፍታም ቢሆን ለድርድር አያቀርቡም" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ "በአድዋ ድልም የታየው ይሄው ህብረታችንና ከብረት የጠነከረ የአንድነታችን ማህተብ ነው" ብለዋል።
"የአሁኑ ትውልድ ከዚህ የምንማረው ትልቅ ቁም ነገር ቢኖር አንድነታችንን አጠናክረን መንቀሳቀስ ከቻልን የሚገዳደረን ሃይል እንደሌለ ነው" ሲሉ ።
አሁንም የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመዳፈር የሚቋምጡ አካላት ካሉ በአድዋ የታየው ፍጹም የሀገር ፍቅርና ወኔ በዚህ ትውልድም እንደሚደገም አረጋግጠዋል።
"በተለይ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታና ሀገራችንን ለማፍረስ የሚፈልጉ ሁሉ ከአድዋ ድል ተማሩ ማለት እንፈልጋለን" ብለዋል።
"አሁን ላይ ያልተሻገርናቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉ" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ "በተለይ ድህነትን ለማሸነፍ እንዲሁም አካባቢያችንን ሰርተን ለመለወጥና ለማበልጸግ ልንተጋ ይገባል " ሲሉ አስገንዝበዋል።
በበአሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ቡዝነሽ መሠረት በበኩላቸው የአድዋ ድል በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና በአፍሪካም የነፃነት ትግልን ያቀጣጠለ መሆኑን ገልፀዋል።
"ድሉ የነጮች የበላይነትና የጥቁሮች የበታችነት አመለካከት ተረት ያደረገና በየትኛውም ዓለም የሚገኙ ጥቁሮች አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ ያስቻለ ነው " ብለዋል።
የጥንት አባቶቻችን ለሀገር አንድ ሆነው እንደተነሱት ሁሉ የዛሬውም ትውልድ ለሀገር ሰላምና ልማት እንዲሁም ከውስጥና ከውጭ ለሚያጋጥመን ፈተና በአንድነት መቆም እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል።
ከበአሉ ተሳታፊዎች መካከል በሲዳማ ክልል የሸበዲኖ ወረዳ ነዋሪ አቶ ተሰማ ለ በሰጡት አስተያየት የአድዋ ድል ከኢትዮጵያውያን አልፎ የመላ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ትግል ምሳሌና የኩራት ምንጭ መሆኑን በመረዳት የአሁኑ ትውልድ ከመከፋፈልና ከመገፋፋት በመራቅ የአባቶቹን ፈለግ እንዲከተል አሳስበዋል።
የምእራብ አርሲ ዞን ነዋሪ አቶ ቁፋ ጎቤ የአድዋ ድል በመላ ዓለም በቀኝ ግዛት ሲማቅቁ ለነበሩ ህዝቦች አንፀባራቂ ድል እንደነበር አስታውሰው "አሁን ላይ በዓሉን ስናከብር ሀገራችንን ቀፍድዶ ከያዛት ዘረኝነትና ጥላቻ ለመላቀቅ ሁላችንም ልንጠነቀቅ ይገባል" ብለዋል።
የሐዋሳ ከተማ ነዋሪና የአርበኛ ልጅ ወይዘሮ ምንታምር ደረስክ በበኩላቸው የጥንት አርበኞች ለሃገር ነጻነት፣ አንድነትና ክብር ሲሉ ተጋድለው አኩሪ ድል እንደተቀዳጁት ሁሉ የአሁንም ትውልድ ሀገራችንን ለመውረር እየተፍጨረጨሩ ያሉትን ኃይሎች አጥብቆ ሊታገላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዓሉን በማስመልከት በአድዋ ድል ዙሪያ የሚያጠነጥን ሰነድ በምሁራን ቀርቦ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን የሲዳማን ህዝብ ቱባ ባህልና እሴት የሚያንፀባርቁ አልባሳትና ቁሳቁሶች ለኤግዝቤሽን ቀርበዋል።
እንዲሁም በስነግጥምና በአጭር ተውኔት አዝናኝና አስተማሪ ትእይንቶች ቀርበው በአሉ በደማቅ ስነ ሥርዐት ተከብሮ ውሏል።
በበዓሉ ላይም አጎራባች ክልሎች፣ ከክልሉ የተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ፣ከፍተኛ አመራሮችና የክብር እንግዶች ተሳትፈዋል።