የድሬዳዋው የግማሽ ማራቶን ውድድር በኦሮሚያ አትሌቶች አሸናፊነት ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋው የግማሽ ማራቶን ውድድር በኦሮሚያ አትሌቶች አሸናፊነት ተጠናቀቀ
ድሬዳዋ የካቲት 14/2013 (ኢዜአ) አለም አቀፍ ዝና ያላቸው የአገራችን አትሌቶች የተሣተፉበትና ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ የተኪያሄደው 14ተኛ የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር በኦሮሚያ ክልልና በኦሮሚያ ፖሊስ ክለብ የበላይነት ተጠናቀቀ ፡፡
ስፖርት ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና እንዲሁም ለአገር ገጽታና አንድነት እንዲውል በስፖርት መሠረተ-ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የድሬዳዋ አስተዳደር አስታውቋል፡፡
ዛሬ መነሻውን በብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት አድርጎ የድሬዳዋን ዋና ዋና ጎዳናዎች ባካለለው የኢትዮጵያ የግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ 5 ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ 14 ክለቦችና የግል ተወዳዳሪ ተካፍለዋል፡፡
ከአጠቃላይ 234 የውድድሩ ተሳታፊዎች 102ቱ ሴቶች በሆኑበት በዚህ መድረክ በሴቶች በተደረገው ውድድር የፌደራል ማረሚያ ቤቷ አትሌት ሰምበሬ ተፈሪ በአንደኝነት ስታጠናቅቅ የኤልሚ አለንዶ ክለብ ተወዳዳሪ ህይወት ገብረኪዳን 2ተኛ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ፈታው ዘራይ ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡
በወንዶቹ ምድብ ደግሞ ከሶስት አመት በፊት በአፍሪካ ሻንፒዮን 2ተኛ የወጣው የኦሮሚያ ፖሊስ ክለብ አትሌት ሉኡል ገብረየስ በበላይነት ሲያጠናቅቅ የክለብ አጋሩ ሲሳይ ለማ ሁለተኛና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ በላይ ጥላሁን ሶስተኛ ሆነው አሽንፈዋል፡፡
በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ለወጡት ከ25 ሺ ብር እስከ 6 ሺ ብር የተሸለሙ ሲሆን ከአንድ እስከ ሶስተኛ ለሆኑት አሸናፊዎች የወርቅ፣የብርና የነሀስ መዳሊያ ተሸልመዋል፡፡
የዘንድሮውን 14ተኛ የኢትዮጵያ የግማሽ ማራቶን ውድድር በሴቶች ዘርፍ በቡድን 40 ነጥብ በማምጣት ኦሮሚያ ክልል አንደኛ በመውጣት የዋንጫ አሸናፊ ሲሆን በወንዶች ደግሞ በ29 ነጥብ የኦሮሚያ ፖሊስ ክለብ ግንባር ቀደም በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
ውድድሩን ላሸነፉ፡ ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት የሜዳሊያ፣ የገንዘብ፣ የምስክር ወረቀት የሰጡት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን አመራሮችና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ናቸው፡፡
ለአሸናፊዎቹ ዋንጫ የሸለሙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንዱትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት፤ ስፖርትን ለሀገር ብልጽግናና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ለማዋል የሚደረገው ተጠናክሮ ይቀጥላለ።
ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ ለወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና መሰረተ-ልማቶች ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በተለይ ስፖርት በህዝቦች መካከል ፍቅርና አንድነት የሚያፈልቅ ልዩ ምትሃታዊ ኃይል ያለው ዘርፍ መሆኑን ተናግረው ስፖርትን መደገፍና ማሳደግ ወጣቱን ከአልባሌ ስፍራዎች መጠበቅ ብቻ ሣይሆን የሀገር ብልጽግና ማሳኪያ ጎዳና እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የሴቶቹ ውድድር ያሸነፈችው አትሌት ሰምበሬ ተፈሪ የድሬዳዋ ሞቃታማ አየርና ረባዳማ ቦታ በውድድሩ ላይ ተፅዕኖ ሣይሆን ምቾት አንደሰጣት ገልፃለች፡፡
በቀጣይ ከኮሮና ራስን በመጠበቅ አገርንና ሰንደቅ አላማን በአለም አደባባይ ለማውለብለብ መዘጋጀቷን ነው የተናገረችው ፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፀሐፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ የድሬዳዋ አስተዳደር፣ የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽንና የድሬዳዋ ህብረተሰብ ለውድድሩ መሳካት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።