ቀጥታ፡

ታማኝ በየነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደዜጋ በመተከልና ትግራይ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች አለኝታነቱን ማሳየት እንደሚገባው ተናገረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13/2013 ( ኢዜአ)  ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደዜጋ በመተከልና በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች አለኝታነቱን ማሳየት አለበት ሲል አርቲስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነ ጥሪ አቀረበ።

በድጋፉ ከአገር ውስጥ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ፤ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ከ170 ሺህ ዶላር በላይ ጥሬ ገንዘብ መሰብሰቡ ተገልጿል።

በትግራይ ክልል በህግ ማስከበር በመተከል ደግሞ በግጭትና አለመረጋጋት በርካታ ንጹሃን ዜጎች ድጋፍ እንደሚሹ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም በርካታ ድጋፍ ሰጭ አካላትና ድርጅቶች ለዜጎች አለኝታ በመሆን ደራሽነታቸው እያሳዩ ይገኛል።

በጣይቱ ሆቴልም "ሰብዓዊነትና ፍቅር፤ ለትግራይና መተከል" በሚል መሪ ሃሳብ ጉዞ አድዋ፣ ለትግራይ እርዳታ አሰባሰብ በጎ ፈቃደኛ፣ አለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት፣ የኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞች እና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ማህበር በጋራ ድጋፍ ማሰባሰብ ከጀመሩ ቀናት አልፏል።

የድጋፍ ጥሪውን ተከትሎም በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የገንዘብ፣ የአልባሳት የምግብ እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል።

የድጋፍ አሰባሰብ አስተባባሪ አርቲስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነ፤ የተቸገሩ ዜጎችን መደገፍ የአንድ ወገን አይደለምና ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኔነት ስሜት ችግራቸውን መጋራት ይኖርበታል ብሏል።

የዜጎችን መከፋት ለመጋራት የተጀመረው የድጋፍ ማሰባሰብ መርሃ ግብር የተለያዩ አካውንቶች ተከፍተው አገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያዊን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጿል።

በድጋፉም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከ170 ሺህ ዶላር በላይ፤ በአገር ውስጥ ካሉ ደግሞ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ መሰብሰቡን ተናግሯል።

በቁሳቁስ ማሰባሰብ መርሃ ግብሩ የተለያዩ የምግብና አልባሳት ድጋፎችም እንዲሁ ተጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቁሟል።

ህብረተሰቡ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጸው ታማኝ መገናኛ ብዙኃን የድጋፍ ሂደቱን በማስተጋባት የዘገባ ሽፋን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።

ለኃይማኖት ተቋማት የተደረገውን ጥሪ ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባቶች በዛሬው እለት ድጋፍ በማድረግ ለምእመኖች መልዕክት ማስተላለፋቸውን አስረድቷል።

በሚቀጥሉት ቀናት ደግሞ የእስልምና፣ የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንትና ሌሎች ኃይማኖት አባቶች ድጋፍ በማድረግ አባታዊ መልእክታቸውን እንደሚያስተላለፉ ይጠበቃል ብሏል።

በቀጣዩ የሳምንት ቀናቶች ደግሞ የስፖርት ሰዎች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ባለሃብቶች እና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንደ ዜጋ ለወገን አለኝታነታቸውን እንደሚያሳዩ ተናግሯል።

ድጋፍ ለማድረግ የተገኙት መጋቢ ኃዲስ እሸቱ ዓለማየሁ እንዳሉት በሃይማኖት እኖራለሁ የሚል ሁሉ ለፈጣሪውና ለወንድሙ በመኖር ለተቸገሩ ወገኖች ካለው ማካፈል እንደሚኖርበት መክረዋል።

ድጋፍ ሲያደርግ ያገኘነው ቢኒያም ወልደጊዮርጊስ በበኩሉ ሰብዓዊነት ከሁሉም በላይ ነውና ሁሉም ዜጋ ካለው ላይ ለተቸገሩ ወገኖቹ በማካፈል አለኝታ መሆን እንዳለበት ጥሪ አቅርቧል።

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጣይቱ ሆቴል ከሚገኘው ጊዜያዊ ማሰባሰቢያ ስፍራ በመገኘት እና በተከፈቱ የገንዘብ ማሰባሰቢያ አካውንቶች  እንደ ቤተሰብና ዜጋ ለወገኑ ደራሽ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል።

ከተሰበሰቡ የገንዘብ፣ የምግብና አልባሳት ቁሳቁሶች መካከል ለህጻናት ምግብ የሚውሉና ለሴቶች ንጽህና መጠበቂያ የሚውሉት ተደራሽ እንዲሆኑ እየተደረገ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

ለወገኖቹ ድጋፍ ማድረግ ለሚሻ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ስም በተከፈተ የሒሳብ ቁጥር “1000327016559” ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም