ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ
አዲስ አበባ ሀምሌ 19/2010 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዴህ)፣ የአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) እና የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) በኢንጂነሩ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልፀዋል። የኢንጂነሩ የሞት ዜና መስማት አስደንጋጭና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያሳዘነ ክስተት መሆኑንም ተናግረዋል። መንግስት የኢንጂነሩን አሟሟት አጣርቶ እልባት እንዲሰጥና በፍጥነት ለህዝብ እንዲያሳውቅም ጠይቀዋል ፓርቲዎቹ። ፓርቲዎቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት የሀዘን መግለጫ ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጆች እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን መፅናናትን ተመኝተዋል። ኢንጅነሩ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ከመላው ኢትዮጵያውያን የተሰጣቸውን ሓላፊነት ይዘው የህዳሴውን ግድብ እውን ለማድረግ ያደረጉት አስተዋፅኦ በታሪክ እየተወሳ የሚኖር ነውም ብለዋል ፓርቲዎቹ።