ቀጥታ፡

ለስድስተኛ ጊዜ የሚደረገው የ2013 አገራዊ ምርጫ ለይስሙላ ሳይሆን ሐቀኛ ምርጫ የመሆን ተስፋ አለው- ኢዜማ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13/2013 ( ኢዜአ)  ለስድስተኛ ጊዜ የሚደረገው የ2013 አገራዊ ምርጫ ለይስሙላ ሳይሆን ሐቀኛ ምርጫ ለማድረግ የተሻለ ተስፋ አለ ብሎ እንደሚያምን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ/ኢዜማ/ አስታወቀ።

ፓርቲው በሕዝብ ቢመረጥ ሕገ መንግስት እንደሚያሻሽልና የዘውግ ፖለቲካን እንደሚለውጥ ዛሬ ባካሄደው የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ይፋ አድርጓል።


የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ/ኢዜማ 'ንቁ ዜጋ፤ ምቹ አገር' በሚል መሪ ሀሳብ የፓርቲው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ዕጩዎችና ደጋፊዎች በተገኙበት የምርጫ ቅስቀሳ ማስተዋወቂያ መርሃ-ግብር አካሂዷል።

የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ መርሐ-ግብሩን ሲከፍቱ እንዳሉት ፓርቲው በ2013 ምርጫ በሰው ኃይል አደረጃጀት፣ በፖሊሲና በሌሎችም በቂ ዝግጅት አድርጓል።

በመሆኑም ፓርቲው ቢመረጥ አገሪቱን ማስተዳደር እንደሚችል ለማሳየት ዛሬ በይፋ የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ማካሄዱን ገልጸዋል።

መጪው ምርጫ ዜጎች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት የምንጥልበትና አገሪቱ ወደ ተረጋጋ ስርዓት የምትሸጋገርበት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

ፓርቲው ምርጫው ነፃና ፍትሀዊ እንዲሆን፣ ፖለቲከኞች በነፃነት በመላ አገሪቱ እንዲንቀሳቀሱ፣ ዜጎች የፈለጉትን ፓርቲ የሚመርጡበትና እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉ ተቋማት የፖለቲካ ድርጅቶችን በእኩል ዐይን የሚመለከቱበት እንዲሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ፍትሃዊ፣ ተዓማኒና እውነተኛ ምርጫ ተደርጎ እንዳማያውቅ ገልጸዋል።

በ1997ቱ አገራዊ ምርጫ በአንጻራዊነት የተሻለ ቢመስልም በወቅቱ ገዥ መንግስት የህዝብ ድምጽ ባለማክበሩ ውጤታማ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

ዘንድሮ ግን እስካሁን ከተደረጉ ምርጫዎች የተለየ ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ መራጩ ህዝብ፣ ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ካለፉት ምርጫዎች ስህተት ከተማሩ የተሻለ ተስፋ እንዳለ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ኢዜማ እስካሁን ከተደረጉ የይስሙላ ምርጫዎች በተለየ ሐቀኛ ምርጫ ለማድረግ ዕድል አለ ብሎ እንደሚያምን ነው የተናገሩት።

በምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ በፓርቲው ማኒፌስቶና የእስካሁን ዝግጅቱ ገለጻዎች የቀረቡ ሲሆን ኢዜማ 440 በላይ የምክር ቤት ዕጩዎችን ስለማዘጋጀቱ ተወስቷል።

ፓርቲው ችግሮችን ከማውሳት ባለፈ ኢትዮጵያ ለገባችበት አሁናዊ ችግር መፍትሔ የሚሆኑ በባህል፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በውጭ ግንኙነት 42 ፖሊሲዎች መቅረጹን ገልጿል።

የኢትዮጵያ አሁናዊ ችግሮች መንስዔ ላለፉት 50 ዓመታት አገራዊ አንድነት እንዲላላ በመሰራቱ፣ ለዚህም ሕወሃት መራሹ መንግስት ህገ መንግስታዊ መዋቅር ሰጥቶ የዘረጋው የዘውግ ፖለቲካ ነው ይላል ፓርቲው።

በመሆኑም ፓርቲው በሕዝብ ቢመረጥ ዜጎች በአገራቸው ባይተዋር ያደረገ 'አፓርታይድ' ያለውና ለአሁናዊ አገራዊ ችግር የዳረገው ሕገ መንግስት እንደሚያሻሽል አረጋግጧል።

የዘውግ ፖለቲካን በዜግነት ፖለቲካ በመለወጥ በቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖትና ብሔር ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ወጥተው ዜጎች በራሳቸው ፍላጎት ማንነታቸውን የሚያዳብሩበት ስርዓት ለመገንባት እንደሚሰራ ገልጿል።

የመሬት ባለቤትነት ችግርን በመቀየርና የሰራተኞች የደሞዝ መነሻ በመቁረጥም ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት እንዲሚሰራ ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም