ምክር ቤቱ የጥናት ውጤቶቹን ወደ ተግባር በመቀየር አሰራርና አደረጃጀቱን ያሻሽላል... አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የጥናት ውጤቶቹን ወደ ተግባር በመቀየር አሰራርና አደረጃጀቱን ያሻሽላል... አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2013(ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጀመሪያው ዓመታዊ የፓርላማ ምርምር ኮንፈረንስ የቀረቡትን የጥናት ውጤቶች ተግባራዊ በማድረግ አሰራርና አደረጃጀቱን እንደሚያሻሽል አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አረጋገጡ።
ምክር ቤቱ ከፓርላማ ምርምር መረብ አባል ተቋማት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነትም ተፈራርሟል።
ትናንት በጀመረውና ዛሬ በተጠናቀቀው የፓርላማ ምርምር ኮንፈረንስ የምክር ቤቱን አሰራርና አደረጃጀት ያሻሽላሉ የተባሉ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች ፓርላማው ዴሞክራሲን ከማጠናከር አኳያ ያለው ሚና፣ የፓርላማ የበላይነትና አሁናዊ ሁኔታ፣ በፓርላማ የሴቶች ተሳትፎና ውጤታማነት የሚሉት ይገኙበታል።
በተጨማሪም የፓርላማው የዲፕሎማሲ ሥራ እና ለኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት ፓርላማው ያለው ሚናን የተመለከቱ የጥናት ውጤቶች በተለያያዩ ባለሙያዎች ቀርበዋል።
የጥናት ስራቸውን ካቀረቡት መካከል የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር አቶ ሰለሞን ተፈራ የገዥው ፓርቲ ተፈጥሮና የፓርቲ ስነ-ምግባር በፓርላማው ሥራ ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ ገልጸዋል።
"በህገ መንግስቱ መሰረት አንድ የፓርላማ አባል ተጠሪነቱ ለህገ መንግስቱ፣ ለህዝቡና ለህሊናው ቢሆንም የፓርቲ አባል በመሆኑ ብቻ የፓርቲውን ዓላማ ለማስፈጸም ይገደዳል" ነው ያሉት።
ሌላው የጥናት ጽፉፍ አቅራቢ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ታደሰ መላኩ እንዳሉት ነጻና ገለልተኛ ህግ ተርጓሚ በሌለበት ሁኔታ የህገ-መንግስት የበላይነትን ማረጋገጥ ከባድ ነው።
የፓርላማው የዲፕሎማሲ ስራ ዝቅተኛ መሆን፣ የዘላቂ ልማት ግቦችን ከመከታተልና ከመቆጣጠር አኳያ ያሉ ውስንነቶች፣ የፓርላማው የሴቶች ተሳትፎና ውጤታማነት ዝቅተኛ መሆን በጥናት ከተለዩ ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ።
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የምክር ቤቱን አሰራርና አደረጃጀት ለማሻሻል የቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች ወሳኝ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ምክር ቤቱ የጥናት ውጤቱን ወደ ተግባር ለመቀየር ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በጥናታዊ ጽሁፉ የተመላከቱ የህግ ማሻሻያ የሚጠይቁና ሌሎች ጉዳዮችም በዝርዝር ታይተው ምላሽ እንደሚሰጥባቸውም አመልክተዋል።
በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ ምክር ቤቱና የምርምር መረብ አባል ተቋማት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።