ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በ38 የገጠር ቀበሌዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተጀመረ

ድሬዳዋ፣ የካቲት 13/2013 (ኢዜአ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በ38 ገጠር ቀበሌዎች ከ6 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የሚካሄድ የአፈርና ወሃ ጥበቃ ስራ ዛሬ ተጀመረ።

የአፈርና ወሃ ጥበቃ ስራውን በዋሄል ክላስተር ተገኝተው ያስጀመሩት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ናቸው፡፡

አቶ ከድር በዚህ ወቅት እንዳሉት በባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የተፈጥሮ ሃብት ሚዛንን በመጠበቅ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

የልማት ስራውን በማጠናከር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ አስተዳደሩ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በአሰሊሶ ክላስተር የተገኙት የድሬዳዋ የግብርና ፣ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኢሊያስ አልይ ለስምንተኛ ጊዜ የሚካሄደው ተፋሰስን መሰረት ያደረገ የአፈርና ወሃ ጥበቃ ስራ 2ሺህ 200 ሄክታር የተራቆቱ ስፍራዎችን እንደሚሸፍን ተናግረዋል።

በ4ሺህ ሄክታር ማሳዎች ላይም የተለያዩ የልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው የፀጥታ ችግር በድሬዳዋ የተፋሰስ ሥራ ባይከናወንም ቀደም ሲል ለሰባተኛ ጊዜ የተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የከርሰ ምድር ውሃ በማጎልበት አርሶ አደሩ በመስኖ ልማት እንዲሰማራና የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ አግዟል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አሊያስ ገለጻ የተፋሰስ ልማቱ በመስኖ የሚለማ ከ1ሺ ሄክታር በላይ ተጨማሪ የእርሻ መሬት የተፈጠረበት፣ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረገና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ሥራ ነው፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ በበኩላቸው ልማቱ ድሬዳዋን ከጎርፍ አደጋ የሚታደግና የገጠሩን ህብረተሰብ ከድህነት ለማላቀቅ የላቀ ሚና አለው ብለዋል፡፡

የገጠሩን ህብረተሰብ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ዘርፈ ብዙ ጥረት ለማሳካት አስተዳደሩ ለመስኖ ፕሮጀክቶች አስፈላጊው በጀት ይመደባል ነው ያሉት፡፡

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከተጀመረ ወዲህ የጠፉ ዕፅዋት እየተመለሱና አካባቢው አረንጓዴ እየሆነ የመስኖ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው የተናገሩት ደግሞ የኡላን ኡሉል ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር ኡስማኤል ቢላል ናቸው፡፡

‹‹ለአስር ተደራጅተን ሽንኩርት፣ ቲማንቲም፣ ድንችና ቃሪያ በማምረት በዓመት በትንሹ እስከ መቶ ሺ ብር ከወጪ ቀሪ እየቆጠብን ነው›› ብለዋል፡፡

ስራውን በቅርበት የሚከታተሉት የዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ መምህር ሰለሞን ደበበ በሰጡት አስተያየት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ለአየር ሚዛን መጠበቅና ለአርሶ አደሩ ልማት መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

የሚሰሩ ልማቶች ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግና የለሙትን በመንከባከብ በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን በቶሎ መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም