ቀጥታ፡

ሀገር አቀፍ የግማሽ ማራቶን ውድድር ነገ በድሬዳዋ ይካሄዳል

ድሬዳዋ፣ የካቲት 13/2013(ኢዜአ) ታዋቂ አትሌቶች የሚካፈሉበት 14ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር ነገ በድሬዳዋ አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን አስታወቀ።

የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ አባልና የአትሌቶች ፕሬዝዳንት ኮማንደር ማርቆስ ገነቴ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት በውድድሩ አምስት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም 14 ክለቦችና የግል ተወዳዳሪዎች በሁለቱም ፆታዎች ይሳተፋሉ፡፡

የውድድሩ ዓላማ በክልሎች፣ ከተሞችና ክለቦች የሚገኙ አትሌቶች የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ዕድል ለመስጠት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በውድድሩ ላይ አለም አቀፍ ዝና ያላቸውን አትሌቶች ጨምሮ 234 አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከመካከላቸውም 102 ሴቶች ይገኙበታል፡፡

ውድድሩ ነገ ጠዋት መነሻውን ብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት አድርጎ የከተማውን ዋና ዋና ጎዳናዎች 21 ኪሎ ሜትር የሚያካልል ይሆናል፡፡

ኮማንደር ማርቆስ ውድድሩ በክልል ከተሞች መደረጉ ተተኪ ስፖርተኞችንም ለማፍራት ያግዛል ብለዋል፡፡

የዘንድሮ ውድድር ከ125ኛው የአድዋ ድል ጋር መገናኘቱ የተለየ ድምቀትና ውበት ያላብሰዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ውድድሩን ለማስተናገድ ላደረገው ዝግጅት አመስግነው ነዋሪዎችም ኮሮናን መከላከያ መንገዶች በመጠቀም ውድድሩን በስፍራው ተገኝተው እንደሚመለከቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውድድሩ ከአንደኛ እስክ ሶስተኛ ደረጃ ለሚወጡት አትሌቶች የሜዳሊያ፣ እስከ 6ኛ ለሚወጡት ደግሞ የገንዘብ ሽልማት ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

አንደኛ ለሚወጡት አትሌቶች ዋንጫ እንደሚሸለሙም ታውቋል፡፡

በውድድሩ አማራ ፖሊስ፣ መከላከያ፣ ፌደራል ማረሚያ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ፌደራል ፖሊስ ፣ ኦሮሚያ ፖሊስ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለቦችና አትሌቶች ጭምር በግላቸው የሚወዳደሩ አትሌቶች ተሣታፊ እንደሚሆኑ ተመልክቷል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ሻኪር አህመድ ለድሬዳዋ አትሌቲክስና ለአትሌቶች ከፍተኛ መነቃቃት ለሚፈጥረው የሩጫ ውድድር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም