ኢዜማ የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩን በግዮን ሆቴል እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜማ የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩን በግዮን ሆቴል እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ /ኢዜማ/ የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩን በግዮን ሆቴል እያካሔደ ነው።
'ንቁ ዜጋ፤ ምቹ አገር' በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው የማስተዋወቂያ መርሃ-ግብር የፓርቲው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ተወዳዳሪ ዕጩዎችና ደጋፊዎች ታድመዋል።
የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ መርሐ-ግብሩን ሲከፍቱ እንዳሉት ፓርቲው በ2013 ምርጫ በሰው ኃይል አደረጃጀት፣ በፖሊሲና በሌሎችም በቂ ዝግጀት አድርጓል።
ፓርቲው ቢመረጥ አገሪቱን ማስተዳደር እንደሚችል ለማሳየት ዛሬ በይፋ የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር እያካሄደ ነው ብለዋል።
መጪው ምርጫ ዜጎች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት የምንጥልበትና አገሪቱ ወደተረጋጋ ስርዓት የምትሸጋገርበት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
ፓርቲው ምርጫው ነፃና ፍትሀዊ እንዲሆን፣ ፖለቲከኞች በነፃነት በመላ አገሪቱ እንዲንቀሳቀሱ፣ ዜጎች የፈለጉትን ፓርቲ የሚመርጡበትና እንደምርጫ ቦርድ ያሉ ተቋማት የፖለቲካ ድርጅቶችን በእኩል ዐይን የሚመለከቱበት እንዲሆን ይፈልጋል ፤ለዚህም ቁርጠኝነት አለው ብለዋል።