ከ11 ሺህ ለሚበልጡ የተለያዩ ምርቶችና አገልግሎቶች ደረጃ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ከ11 ሺህ ለሚበልጡ የተለያዩ ምርቶችና አገልግሎቶች ደረጃ ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13/2013(ኢዜአ) የምርትና አገልግሎት ጥራት እንዲጠበቅ ለ11 ሺህ 485 የተለያዩ ምርቶችና አገልግሎቶች ደረጃዎች መስጠቱን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው በ300 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የደረጃዎች አካዳሚ በቅርቡ እንደሚመረቅም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት ኤጀንሲው በህግ የተሰጠውን ሥልጣን መሰረት በማድረግ በአገሪቱ ለሚመረቱና ለሚሰጡ አገልግሎቶች ደረጃዎች ይሰጣል።
በዚህም ተቋሙ እንደ ኤጀንሲ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በ11 ሺህ 487 ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ አስፈላጊውን የደረጃዎች ምርመራና ጥናት በማድረግ ደረጃ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ለ285 ምርቶችና አገልግሎቶች ደረጃዎች መስጠቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በአጠቃላይ ከተሰጡት ደረጃዎች መካከል 256ቱ አስገዳጅ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ኤጀንሲው በተለይ በአስገዳጅነት ከሰጣቸው ደረጃዎች መካከል ከህብረተሰብ ጤናና ደህንነት ጋር የተያያዙ፣ የግብርና፣ የኮንስትራክሽን፣ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የውሃ ምርቶች ይገኙበታል፡፡
ህብረተሰቡ ለጥራትና ደረጃዎች ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን በመስራት ላይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አቶ እንዳለው እንደገለጹት ተቋሙ ደረጃዎችን ከማውጣትና ከመስጠት ባለፈ በጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በአገሪቱ ጎልተው የሚታዩ ችግሮችን በመለየት ለመፍትሄው ይሰራል፡፡
በኢትዮጵያ የሚታየውን የቆሻሻ አወጋገድ ተግባር በተለያዩ መስፈርቶች በመለየት ደረጃዎችን እያወጣ መሆኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል።
ደረቅ ቆሻሻን ከመነሻው በአግባቡ ወደ ሀብትነት መቀየር እንደሚቻል ለህብረተሰቡ የማስገንዘብ ሥራዎች በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸው ይከናወናሉ።
የፋይናንስ ተቋማትን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችሉ 28 ደረጃዎች መዘጋጀታቸውንም አቶ እንዳለው አመልክተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የጤና ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ከዘመኑ ጋር ለማራመድ እንዲችሉ ከ70 በላይ ደረጃዎችን ለተቋማቱ ማውጣቱንና ወደተግባር ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ተናግረዋል።
ኤጀንሲው ይህን ሥራውን ለማሳለጥ በ300 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው ዘመናዊ የደረጃ አካዳሚ ግንባታ በቅርቡ ተጠናቆ እንደሚመረቅ ተናግረዋል፡፡
"አካዳሚው ለኤጀንሲው ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ማንኛውንም ደረጃ የሚመለከቱ ሥራዎች ይከናወኑበታል" ብለዋል።
ለዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣ ለማምረቻ ተቋማት፣ ለምርምር ተቋማት፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለተለያዩ ደረጃን ለማወቅ ለሚፈልጉ አካላት ከደረጃ ጋር በተያያዘ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥም አመልክተዋል፡፡
አካዳሚው በአገሪቱ ከስልጠና ጋር የሚነሱ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ በምስራቅ አፍሪካ ካሉ መሰል ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት እገዛ እንደሚያደርግ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ለምርቶችና አገልግሎቶች ደረጃዎችን መስጠት የምርትና አገልግሎት ጥራትን ደረጃ ከማሻሻል ባለፈ በጥራት ዙሪያ ሊፈጠሩ የሚችሉ የተለያዩ ችግሮችን ቀድሞ በመከላከል ህዝብና አገርን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻልም አስረድተዋል።