ቀጥታ፡

በመተከል ዞን የሚኖሩትን የብሔረሰቦች ስብጥር መሰረት ያደረገ የአመራር ሽግሽግ እየተደረገ ነው-ግብረ ኃይሉ

የካቲት 13/2013 ( ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉምዝ መተከል ዞን የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችን ስብጥር መሰረት ያደረገ የአመራር ሽግሽግ እየተደረገ መሆኑን በአካባቢው የተሰማራው የተቀናጀ ግብረ ኃይል ገለጸ።

በዞኑ ጸጥታን እያስከበረ የሚገኘው የተቀናጀ ግብረ ኃይል አባላት በዳንጉር፣ ማንዱራ፣ ወምበራ፣ ቡለንና ድባጤ ወረዳዎች የተደረገውን የአመራር ሽግሽግ ተመልክቶ ለአመራሮቹ የሥራ መመሪያ ሰጥቷል።

ከዚህ በፊት የነበረው የአመራር ስብጥር በአመዛኙ በዞኑ የሚኖሩትን ብሔር/ብሔረሰቦች ታሳቢ ያላደረገ እንደነበር ተመልክቷል።

ይህም በዞኑ የጸጥታ ችግር እንዲባባስና የተወሰነ አካል ተጎጂ እንዲሆን ማድረጉን ግብረ ኃይሉ ገልጿል።

በዞኑ ጸጥታ እያስከበረ የሚገኘው ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አሥራት ዴኔሮ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት አሁን የመጣው አመራር በዞኑ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር መስራት ይጠበቅበታል።

በዞኑ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሕዝቡን በእኩልነት ለማገልገል አዲሱ አመራር ራሱን ማዘጋጀት አለበት ብለዋል።

አመራሩ እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ሕዝቡን በማግኘት ችግሮቹን ለመፍታት እንዲሰራ አስተባባሪው አሳስበዋል።

ከሁሉም በላይ አመራሩ ከጎሰኝነትና ዘረኝነት ወጥቶ በዞኑ የሚኖሩትን ሁሉንም ነዋሪዎች በእኩልነት ማገልገል ይጠበቅበታል ብለዋል።

በዞኑ የተፈጸሙ አንዳንድ ተግባራት ከሰው ልጆች የማይጠበቁ በመሆናቸው መወገዝ እንደሚገባቸው ሌተናል ጄኔራል አሥራት አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም አሁን ወደ ስራ የሚገባው አመራር ከብልሹ አሰራርና ከሱስ የጸዳ እንዲሁም በስነ ምግባር የታነጸ ሆኖ ሕዝቡን እንዲያገለግል ጥሪ አቅርበዋል።

አዲሱ አመራር በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕዝብ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት፣ ሕዝቡን ማስታረቅና ተፈናቃይ ወገኖችን ወደ ህዝቡ መቀላቀል እንዳለበትም አቅጣጫ አስቀምጠዋል ሌተናል ጄኔራሉ።

የግብረ ኃይሉ አባልና የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው ከምንም በላይ ወደ ሥራ የሚገባው የአመራር ቡድን ሕዝብን በእኩልነትና በክብር ለማገልገል እንዲዘጋጅ መክረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ሰላምና ደህንነትን ማስጠበቅ፣ ሕዝቡን ያለ አድልኦ ማገልገል፣ ሕግን ማክበርና ማስከበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ከዚህ ባለፈ አመራሩ ተግባር ተኮር መሆን፣ በመንግሥትም በሕዝብም ዘንድ መታመን፣ ከሌብነት፣ ከውሸትና ከማጭበርበር ታቅቦ ሕዝብን ማገልገል ይኖርበታል ሲሉ አስገንዝበዋል።

አዲስ የተመደቡ አመራሮችም ሕዝቡ ከምንም በላይ ከአድልኦ በጸዳ መልኩ መንግሥታዊ አገልግሎት እንድንሰጠው ይፈልጋል ብለዋል።

ሕዝቡም ጥያቄውን በግልጽ ማቅረቡን የገለጹት አመራሮቹ፣ እነርሱም በሚችሉት ሁሉ ሕዝቡን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም