ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ በኤሌክትሪክ አሰጣጥና ስርጭት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በቅንጅት የሚፈታ ፎረም ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13/2013 ( ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥና ስርጭት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመገምገም በቅንጅት የሚፈታ ፎረም ተመሰረተ።

ፎረሙ በከተማ አስተዳደር፣ በሪጂንና በዲስትሪክቶች መካከል ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር በየአካባቢው የሚፈጠሩ ችግሮችን በመገምገምና በመወያየት መፍታት ያስችላል ተብሏል።

ፎረሙ የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን፣ የከተማ አስተዳደሩንና የሚመለከታቸውን አካላት በመያዝ በከተማና በክፍለ ከተማ ደረጃ የሚቋቋም መሆኑ ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ደረጃ የሚቋቋመው ፎረም በከተማዋ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰብሳቢነት የሚደራጅ ሲሆን በተመሳሳይ በክፍለ ከተማ ደረጃ የሚኖረው በዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰብሳቢነት የሚንቀሳቀስ ይሆናል።

ፎረሙ ሲመሰረት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይን ጨምሮ የአስተዳደሩ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የከተማ አስተዳደሩና የክፍለ ከተማ ሥራ አስፈፃሚዎች ተገኝተዋል።

ለውይይት መነሻ በቀረበው ሰነድ በአስተዳደሩ የኤሌክትሪክ አሰጣጥና ስርጭት ላይ በክፍለ ከተማና በተቋማት የተለዩ ችግሮች ተዳሰዋል።

በክፍለ ከተማ ደረጃ እንደ ችግር ተለይተው ከተነሱት መካከል የኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ የመንገድ ዳር መብራት አለመኖር፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማነስና መብዛት፣ የአዳዲስ ደንበኞች የትራንስፎርመርና የቆጣሪ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ማጣት የሚሉት ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም የመሰረተ ልማት አለመሟላት ፣ የአደጋ ተጋላጭነት እና የተቋሙ እና የህዝብ ውይይት አለመኖር የሚሉት ይገኙበታል።

ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በተያያዘም የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለሥልጣን፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል መቆጣጠር ባለስልጣን፣ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም መንገዶች ባለስልጣን ችግሮች እንዳሉ ማንሳታቸው በሰነዱ ተጠቅሷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በከተማ አስተዳደሩ ከመብራት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚነሱ ችግሮች እንዳሉ ገልጸዋል።

"መንግስት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ከመፍታት አንፃር በተለይ አንገብጋቢ የሆነውን የህዝብ ችግር በቅንጀት ለመፍታት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።

ፎረሙ በየክፍለ ከተማው ከሚገኙ አመራሮች ጋር ችግሮቹን በቅንጅት ለመፍታት እንደሚያስችልም አቶ ጃንጥራር አመልክተዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው "በክፍለ ከተማ ደረጃ ፎረሙ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ መግባት እንዳለበት የሥራ አቅጣጫ ተሰጥቷል" ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ፎረሙ በአገልግሎት አሰጣጥ እና ስርጭት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ነው የገለጹት ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም