የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 10 ሺህ ሠራተኞቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቤት አቅርቦት መርሀ-ግብር ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 10 ሺህ ሠራተኞቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቤት አቅርቦት መርሀ-ግብር ይፋ አደረገ
ሀዋሳ ፤ የካቲት 12/2013 (ኢዜአ) የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 10 ሺህ ሠራተኞቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ የኪራይ ቤት አቅርቦት መርሀ-ግብር ይፋ አደረገ።
መርሀ-ግብሩ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ይፋ ሲደረግ የፓርኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ከተማ እንዳሉት ሠራተኞች ከመኖሪያ ቤት ዕጥረት የተነሳ ከፓርኩ ርቀው ለመኖር ይገደዳሉ።
ይህም ሠራተኞችን ለተጨማሪ ወጪና እንግልት ከመዳረጉ ባለፈ ለበርካታ ሰራተኞች ፍልሰት መንሰዔ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ችግር ለማቃለል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ዛሬ ይፋ የተደረገው መርሀ-ግብር ገባራዊ የሚደረገው ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም በፓርኩ አቅራቢያ ከሶስት እስከ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ የሚገኙ ሕጋዊ የቦታ ይዞታ ማረጋገጫ ኖሯቸው የገንዘብ ዕጥረት የሚገጥማቸው ባለንብረቶ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር በማመቻቸት ለሰራተኞች የሚሆኑ የኪራይ ቤቶችን ኢንዲገነቡ ይደረጋል ብለዋል።
10 ሺህ የፓርኩን ሠራተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህ መርሀ-ግብር በአራት ምዕራፎች ተከፍሎ የሚካሄድ መሆኑን አስረድተዋል።
በየአንዳንዱ ምዕራፍ ለ200 ተበዳሪዎች ገንዘብ በማመቻቸት 2 ሺህ 500 ለሚጠጉ ሠራተኞች የኪራይ ቤቶችን እንዲገነቡ ይደረጋል ብለዋል።
የሚገነቡት ቤቶች ለታለመለት ዓላማ ብቻ ሊውሉ የሚችሉና የተጋነነ ዋጋ የማይጠየቅባቸው መሆናቸውን የሚያረጋግጥና የግንባታ ሂደቱንም የሚቆጣጠር የባለድርሻ አካላት የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ የመጀመሪያ ዙር ተበዳሪዎችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ በሀገሪቱ ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ኢንዱሰትሪ መር ኢኮኖሚ የሚደረገውን ሽግግር ከማቀላጠፍ ባለፈ በርካታ የሰው ኃይል በመያዝ ጥልቅ እገዛ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በአንፃሩ የሠራተኞች የመኖሪያ ዕጥረት ደግሞ ሌላኛው የዘርፉ ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንን ችግር ለማቃለል መርሀ-ግብሩ አዲስ የትብብር ዕይታን ይዞ የመጣ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዚህ ሥራ በአጠቃላይ 500 ሚሊዮን ብር ብድር በመመደብ የልማት አጋርነቱን አሳይቷል ብለዋል።
የሥራው አዋጭነቱ እየታየ ወደ ሌሎች ፓርኮች እየሰፋ እንደሚሄድ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ለውጤታማነቱ ሁሉም በትብብር መንፈስ እንዲሰራም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሀዋሳ ከተማ አሰተዳደረ ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋየ ቱኬ በበኩላቸው መርሀ-ግብሩ የፓርኩን ሠራተኞችን ችግር ከመፍታት ባሻገር በከተማዋ ያለውን የቤት አቅርቦት ችግር በማቃለል ትልቅ እፎይታን የሚሰጠን ነው ብለዋል።
ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ ከተማ አስተዳደሩ እስከ ፍፃሜው ድረስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ28 ሺህ በላይ ሠራተኞች እንደሚገኙ ተመልክቷል።