ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የጉዞና የጉብኝት ደህንነት ማረጋገጫ እውቅናዋን ለቱሪዝም ገበያና ትውውቅ መጠቀም ጀምራለች - ቱሪዝም ኢትዮጵያ

አዲስ አበባ የካቲት 12/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ያገኘችውን ዓለም አቀፍ የጉዞና የጉብኝት ደህንነት ማረጋገጫ እውቅና ለቱሪዝም ገበያና ትውውቅ መጠቀም መጀመሯን ቱሪዝም ኢትዮጵያ አስታወቀ።

መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ዓለም አቀፉ የጉዞና ቱሪዝም ምክር ቤት በጥር 2013 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የጉዞና ደህንነት ማረጋገጫ እውቅና መስጠቱ ይታወቃል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ ኢትዮጵያ እውቅናውን ያገኘችው ምክር ቤቱ ያስቀመጣችውን ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች በማሟላቷ እንደሆነ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ የጉዞና ጉብኝት የቱሪዝም ምክር ቤት የኮቪድ-19 መከላከልን መሰረት ያደረገ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ዘርፍ የደህንነት መመሪያ ሰነድ አዘጋጅቶ እንደነበር ተናግረዋል።

አገራትም የምክር ቤቱን ሰነድ መነሻ በማድረግ የራሳቸውን መመሪያ ማዘጋጀት እንደሚችሉ የሚገልጽ በመሆኑ ኢትዮጵያም ይህንኑ ተከትላ የራሷን መመሪያና ስትራቴጂ አዘጋጅታ ወደ ስራ ገብታለች ብለዋል።

በሂደቱ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ምክር ቤቱን መመሪያና ጽንሰ ሀሳቦች በመከተል በትራንስፖርት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና ሆቴሎች ከእንግዳ መቀበያ እስከ ምግብ ማብሰል ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ሲሰራም ቆይቷል።

በቱሪስት መዳረሻዎች የኬሚካል ርጭት መካሄዱን፤ ይህም ምክር ቤቱ ካቀረባቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ካስቀመጣቸው ምክረ ሀሳቦች መካከል ዋንኛው እንደሆነ አቶ ስለሺ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረረሽኝን በመከላከል የቱሪዝም እንቅስቃሴን ለመጀመር በከወነቻቸው ተግባራት ዓለም አቀፍ የጉዞና ጉብኝት ደህንነት ማረጋገጫ እውቅና ማግኘቷን ገልፀዋል።

የደህንነት ማረጋገጫ እውቅናው ቱሪስቶች ደህንነት ተሰምቷቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ መተማመን ከመፍጠር ባለፈ የቱሪዝም መደረሻዎች ንጽህናቸው እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያገኘችውን ዓለም አቀፍ የጉዞና ጉብኝት ደህንነት ማረጋገጫ እውቅና ለቱሪዝም ገበያና ትውውቅ መጠቀም መጀመሯንም አስታውቀዋል።

በእውቅናው አማካኝነት ኢትዮጵያ ቱሪስቶች ደህንነታቸው ከሚጠባቅባቸው ቦታዎች አንዷ መሆኗን የማስተዋወቅ ተግባር በስፋት እንደሚከናወንም አቶ ስለሺ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተሮች አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አንድነት ፈለቀ በበኩላቸው የደህንነት ማረጋገጫ እውቅናው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተጎዳውን የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማነቃቃት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

እውቅናው አስጎብኚ ድርጅቶች ቱሪስቶችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ለማድረግ ለሚያከናውኑት የማስተዋወቅ ስራ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

በቱሪዝም ዘርፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችን በጥብቅ መተግበር ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቱሪዝምና የወጪ ንግድና ቱሪዝም ማስፋፊያ ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ረጋሳ ከፍአለ የደህንነት ማረጋገጫ እውቅናው ጎብኚዎች ጤናቸው ወደሚጠበቅበት ቦታ ለመምጣት ኢትዮጵያን እንዲመርጡ የማድረግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ዓለምአቀፉ የጉዞና ቱሪዝም ምክር ቤት በጥር 2013 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የጉዞና ጉብኝት ደህንነት ማረጋገጫ እውቅና ከሰጣቸው 14 የአፍሪካ አገራት አንዷ ናት።

እውቅናውን ካገኙት የአፍሪካ አገራት መካከል ኬንያ፣ ቱኒዚያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያና ግብጽ ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም