የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኢንጂነር ስመኘው ህልፈተ-ህይወት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኢንጂነር ስመኘው ህልፈተ-ህይወት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ
አዲስ አበባ ሐምሌ 19/2010 የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ህልፈተ-ህይወት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ። ጉባኤው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ኢንጂነሩ አገራቸውንና ሕዝባቸውን በበረሃና በሃሩር እየኖሩ አገልግለዋል። የግድቡ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሰባት ዓመታት 'ደከመኝ ሰለቸኝ' ሳይሉ ሙሉ ጊዜያቸውን በስራቸው ላይ ማሳለፋቸውንም ጠቅሷል። ኢንጂነር ስመኘው የጀመሩት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ያስተባበረ ታላቅ ሐውልት ከመሆኑም በላይ አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት የሚያግዝ መሆኑንም ጉባኤው አመልክቷል። ጉባዔው ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው ኢትዮጵያውያንም መጽናናትን ተመኝቷል። በተያያዘ ዜና የትምህርት ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ዜና ዕረፍት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል። ኢንጂነር ስመኘው የጀመሩትን የህዳሴ ግድብ ከዳር ለማድረስ የሚኒስቴሩ አመራርና ሰራተኞቸ ከመቼውም ጊዜ የላቀ ርብርብ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል። የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በኢንጂነሩ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን መግለፃቸውን እንደቀጠሉ ነው። ኢንጂነር ስመኘው በሚያሽከረክሩት የሰሌዳ ቁጥር “ቪ8” ተሽከርካሪ ውስጥ እንዳሉ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሞተው የተገኙት ዛሬ ጠዋት ነው። የኢንጂነር ስመኘው በቀለን አማሟት ሁኔታ የማጣራት ሥራ መጀመሩን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል ዛሬ ከቀትር በኋላ አስታውቀዋል።