ኢዜማ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቱን አስተዋወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜማ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቱን አስተዋወቀ
የካቲት 12/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ፓርቲ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክትና መሪ ቃል አስተዋወቀ።
ፓርቲው አንደኛ መደበኛ ስብሳባውን ማካሄድ ሲጀምር የመወዳደሪያ ምልክቱ 'ሚዛን' መሪ ቃሉም 'ንቁ ዜጋ ምቹ አገር' መሆኑን ለአባላቱ አስተዋውቋል።
በስብሳባው መክፈቻ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ መጪው ምርጫ አገሪቷን ወደ ተሻለና ወደተረጋጋ ሁኔታ የሚመልስ እንደሚሆን ይታመናል ብለዋል።
ፓርቲያቸውም የተሻለ ተፎካካሪ ሆኖ ለመውጣት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመዋል።
ምርጫ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ እየተካሄደ መሆኑንም አክለዋል።
በስብሰባው የመወዳደሪያ ምልክትና መሪቃል ከማስተዋወቅ ባለፈ የፓርቲውን ፖሊሲ ይፀድቃል፤ ለምርጫ ዝግጅት የተሰሩ ስራዎችም ለዕጩ አባላት ይፋ ይደረጋሉ ብለዋል።
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ መጪውን አገራዊ ምርጫ ስኬታማ ለማድረግ የአገሪቷን ሠላምና ደህንነት ማስከበር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ኢዜማ ለምርጫው አስፈላጊ ግብዓቶችን ከማሟላት ጀምሮ በቂ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ እንዲሆን መንግስት ለሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚገባም አመልክተዋል።
በፓርቲው አንደኛ መደበኛ ስብሰባ ከሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች የተወከሉ ዕጩ ተወዳዳሪዎችና አመራሮቹ ታድመዋል።