''የካቲት 12'' በሽንፈት ቂም ሰማዕትነትን የተቀበሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መታሰቢያ - ኢዜአ አማርኛ
''የካቲት 12'' በሽንፈት ቂም ሰማዕትነትን የተቀበሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መታሰቢያ
የካቲት 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) የሰማዕታት ቀን መታሰቢያ ''የካቲት 12'' በሽንፈት ቂም ሰማዕትነትን የተቀበሉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መታሰቢያ ነው።
ዛሬ የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም 84ኛው የሰማዕታት ቀን መታሰቢያ በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቧል።
ይህ ቀን በተለይ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከማይፋቁ መጥፎ ትዝታዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው።
ፋሺስት ጣሊያን በመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነትና ትብብር አድዋ ላይ ቢሸነፍም የሽንፈቱን ቂም ለመወጣት ዳግም ኢትዮጵያን ለመውረር መምጣቱን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
አርበኞች በዱር በገደል ራሳቸውን እያደራጁ ወራሪውን አላስቆም አላስቀምጥ ማለታቸውንም እንዲሁ።
በተለይም አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉት ወጣቶች በአዲስ አበባ በፋሺስቱ መሪ ግራዚያኒ ላይ የእጅ ቦምብ በመወርወር ለመግደል መሞከራቸው ይጠቀሳል።
ወጣት ስምኦን አደፍርስ ደግሞ ቦምብ የወረወሩት ወጣቶች ከፋሽስቱ እንዲያመልጡ በታክሲ ይዞ በመሸሽ ትልቅ ጀብዱ በመፈጸም ይታወቃል።
የግድያ ሙከራው ያበሳጨው ፋሽስት ጣሊያን በ1929 ዓ.ም ልክ በዛሬዋ ቀን የአዲስ አበባን ነዋሪዎች በግፍ በመጨፍጨፍ የበቀል ጥሙን ተወጥቷል።
ለመሆኑ ይህ የሰማዕታት ቀን መታሰቢያ በመዲናዋ ነዋሪዎች ዘንድ ምን ያህል ይታወቃል? ኢዜአ በበዓሉ የታደሙ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።አስተያየታቸውን የሰጡት የከተማዋ ነዋሪዎች ፋሽስቱ ጣሊያን አስከፊ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ተናግረዋል።
ጭፍጨፋው በአካፋና በዶማ ጭምር የተካሄደና ደም እንደጎርፍ የፈሰሰበት መሆኑን ይዘክራሉ።
"ህጻን ሳይሆን አሮጊት ሳይሆን አጠቃላይ አንድ ቀን ሙሉ ይሄ አልበቃ ብሎ ደብረሊባኖስ ሄዶ መነኮሳቱን፣ መናኞችን ሁሉ ሙሉ ቀን ኢትዮጵያዊያኖችን የፈጀበትን ቀን ነው" ብለዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ ዕለቱን ከአሁናዊ ሁኔታ ጋር በማያያዝም ኢትዮጵያ ላይ ከባድ ግፍና በደል የፈጸመውን ፋሺስት ጣሊያንን ይቅር ያለ ልብ እርስ በርሱ ይቅር መባባል አያዳግተውም ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን በተሳሰተ ትርክት የእርስ በርስ መልካም ግንኙነታቸውን እንዳያሻክሩ፤ ፖለቲከኞችም ሕዝብን ከስልጣናቸው በማስቀደም የሕዝቦችን አንድነት የበለጠ ማጠናከር ላይ እንዲያተኩሩ ጠይቀዋል።
የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት ከ84 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ቀን ከ30 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በፋሺስት ኢጣሊያ ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ከተማዋም በደም ጎርፍ ተጥለቅልቃለች።