ኢትዮጵያ በጥቁር ሕዝቦች ትልቅ ስፍራ ያሰጣትን የአድዋን ድል በሚገባ እያከበረችው አይደለም - የታሪክ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በጥቁር ሕዝቦች ትልቅ ስፍራ ያሰጣትን የአድዋን ድል በሚገባ እያከበረችው አይደለም - የታሪክ ምሁራን
የካቲት 12/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ትልቅ ቦታ ያገኝችበትን የአድዋን ድል በሚገባ እያከበረችው አይደለም ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የታሪክ ምሁራን ገለጹ።
ድሉ ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት እንቅስቃሴ ያለውን አበርክቶ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ አካቶ ማስተማር ይገባልም ብለዋል።
ታሪክ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያዊያን በአድዋ ድል ነጻነታቸውን ያወጁበትና ለጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነውን ድል ያስመዘገቡበት እንደሆነ ያወሳል።
የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው "የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ አድማስ ባሻገር በቅኝ ግዛት ለነበሩ የአፍሪካ ሕዝቦችና በጭቆና ውስጥ ለነበሩ ጥቁር ሕዝቦች ትልቅ ተስፋን የሰጠ ነው" ይላሉ።
የተገኘው ድል የመላ አፍሪካዊነት ወይንም ፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ውስጥ ኢትዮጵያ የመሪነት ሚና እንዲኖራት ማድረጉንም ጠቅሰዋል።
ይሁንና ኢትዮጵያ የአድዋ ድል በአፍሪካዊያን ዘንድ ሊያስቀምጣት በሚገባው ስፍራ ላይ እንደማትገኝና በድሉ ያገኘችውን ትልቅ ቦታ እንዳልተጠቀመችበት ነው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው የገለጹት።
ኢትዮጵያ በድሉ ምክንያት በአፍሪካዊያን ዘንድ ያገኘችውን ቦታ አሳንሳ መመልከት እንደሌለባት የገለጹት የታሪክ ምሁሩ "በአፍሪካ በዲፕሎማሲና በፖለቲካው መስክ ያላትን ሚና ማሳደግ ይጠበቅበታል" ብለዋል።
ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የአድዋ ድል ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት እንቅስቃሴና ለፓን አፍሪካኒዝም ስላበረከተው አስተዋጽኦ ጥናትና ምርምር ማካሄድ እንዳለባቸው ነው የጠቆሙት።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ማካሄድና በዘርፉ የሚሰሩ ተቋማትን መመስረት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያም የረዳት ፕሮፌሰር አበባውን ሃሳብ ይጋራሉ ጥቁር ሕዝቦች ቀና ብለው እንዲሄዱ ላደረጋቸው የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን 'ባይተዋር ነን' ሲሉ ገልፀውታል።
"በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል" እንዲሉ ጥቁር ሕዝቦች የአድዋን ድል ሕያው ተምሳሌት አድርገው ሲያከብሩት ኢትዮጵያዊያን የሚገባውን ክብር እየሰጠነው አይደለም ባይ ናቸው ፕሮፌሰር አህመድ።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ባሳደሩበት ጊዜ የጥቁር ኮንግረስ ጉባኤ ኢትዮጵያን በመደገፍ ያሳየው አጋርነት የአድዋ ድል ለጥቁር ሕዝቦች ያለውን ትልቅ ትርጉም አጉልቶ የሚያሳይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በአሜሪካ የካቲት ወር "የጥቁሮች ወር" በሚል ተሰይሞ የአድዋን ድል የነጻነታቸው ምልክት አድርገው እያከበሩት እንደሚገኝ ጠቁመው ኢትዮጵያም ለበዓሉ አከባበር ትኩረት ልትሰጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር አህመድ ሀሰን የአድዋ ድል ተምሳሌትነት በአፍሪካ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት ጉዳይ ጨው እንደሌለው ወጥ መሆኑን የሚያሳይና በአህጉሩ ያላትን ተቀባይነት ያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።
ጥቁር ሕዝቦች ኢትዮጵያን የነጻነታችን ቤት እንዲሉ ያደረገውን የአድዋን ድል ማስተዋወቅና በተለያዩ ቋንቋዎች ማስተማር እንደሚገባም አመልክተዋል።
የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ ያስገኘውን ክብር እንደ ትልቅ አቅም መጠቀም እንደሚያስፈልግ አክለዋል።
125ኛው የአድዋ ድል በዓል "አድዋ የኅብረብሔራዊ አንድነት አርማ" በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።
የዘንድሮው በዓል ከየካቲት 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን ዝግጅቱን የሚያስተባብርና በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሚመራ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤትም ተቋቁሟል።