ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል ለ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ተደርጓል - አቶ ምትኩ ካሳ

የካቲት 11 ቀን 2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ መደረጉን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ገለጹ።

ይህም ሰብአዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ከቀመጠው አሃዝ የ200 ሺህ ሰው ብልጫ አለው ተብሏል።

በናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ የተሳተፉት የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በትግራይ ክልል ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በፊት የሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን እንደነበር አውስተዋል።

ከሕግ ማስከበር እርምጃው በኋላ በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ቁጥር ለማወቅ የልማት አጋሮችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የመጀመሪያ የዳሰሳ ጥናት መደረጉን አስታውሰዋል።

በጥናቱ መሰረት በክልሉ ተጨማሪ 700 ሺህ ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በመገለጹ በአጠቃላይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።

“በክልሉ እስካሁን ለ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ መደረጉንና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ከቀመጠው አሃዝ በላይ ተጨማሪ 200 ሺህ ሰው ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል” ብለዋል።

በከተሞች አካባቢ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የጠቆሙት አቶ ምትኩ፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ሚሊዮን ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውና የሁለተኛው ዙር ሰብአዊ ድጋፍ በቀጣዩ ሳምንት እንደሚጀመር አመልክተዋል።

በትግራይ ክልል ለሁለት ወራት የሚሆን 84 ሺህ ሜትሪክ ቶን የድጋፍ አቅርቦት እንደሚገኝ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ “በመንግስት ወጪ ከውጭ 300 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በግዢ ሂደት ላይ ይገኛል” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የአልሚ ምግብና የስንዴ ዱቄት በመግዛት በክልሉ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

መንግስት በመቀሌ ካለው የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ማስተባበሪያ ማዕከል በተጨማሪ በሽሬ ከተማ ድጋፍ የሚያስተባበር ማዕከል ማቋቋሙን አመልክተዋል።

በቀጣይ በአድዋ፣ አክሱም፣ አዲግራትና አላማጣ ከተሞች የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ማስተባበሪያ ማዕከላት እንደሚቋቋሙ ጠቁመዋል።

“ከሰብአዊ ድጋፍ ስርጭት አኳያ ከተቀመጠው መመሪያ ውጪ ፍትሐዊ ባልሆነ መልኩ ድጋፍ የማከፋፈል፣ ድጋፍ የጫኑ መኪናዎች በፍጥነት ያለውን አቅርቦት ያለማራገፍና ድጋፍ የጫነ መኪናን አቅጣጫ በማስቀየር የሚፈጸሙ የሌብነት ድርጊቶች እየታዩ ነው” ብለዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ምግብ ነክ ካልሆነ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከ26 መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየተሰራ እንደሚገኝና እስካሁን ለ75 ተቋማት በሰብአዊ ድጋፍ ለሚሰሩ ተቋማት ፈቃድ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

ይሁንና በተወሰኑ ተቋማት ዘንድ ከሰብአዊ ድጋፍ ምንም እሴት የማይጨምር ተግባር እያከናወኑ እንደማይገኝና ይሄም ሊስተካከል እንደሚገባው ነው አቶ ምትኩ የገለጹት።

ከሰብአዊ ድጋፉ በተጨማሪ በትግራይ ክልል ዘላቂ የሰላም ግንባታና መልሶ ማቋቋም ላይ የሚሰራ መንግስትና አጋር አካላትን ያቀፈ ቡድን ተቋቋሞ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮችን ተጠቅሞ በቀጣይ በትግራይ ክልል ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ በየጊዜው ተደራሽ የማድረግ ተግባር እንደሚያከናውን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም