ማንኛውም ሶስተኛ ወገን የኢትዮጵያንና የደቡብ ሱዳንን ግንኙነት ማበላሸት አይችልም- የደቡብ ሱዳን ፖሊስ አገልግሎት ሀላፊ - ኢዜአ አማርኛ
ማንኛውም ሶስተኛ ወገን የኢትዮጵያንና የደቡብ ሱዳንን ግንኙነት ማበላሸት አይችልም- የደቡብ ሱዳን ፖሊስ አገልግሎት ሀላፊ
የካቲት 11/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ነፃነት ያበረከተችውን አስተዋፅኦ ምን ጊዜም እንደማይረሱትና በምንም መለኪያ ማንኛውም ሶስተኛ ወገን የኢትዮጵያንና የደቡብ ሱዳንን ግንኙነት ማበላሸት እንደማይችል የደቡብ ሱዳን ፖሊስ አገልግሎት ሀላፊ ኢንስፔክተር ጀነራል ማጃክ አኬስ አስታወቁ።
የደቡብ ሱዳን ፖሊስ አገልግሎት ሀላፊ ኢንስፔክተር ጀነራል ማጃክ አኬስ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ጋር በሁለቱ ሀገራት የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው በደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ የፖሊስ አገልግሎት ኃላፊ ኢንስፔክተር ጀነራል ማጃክ አኬስ የተመራ የልኡክ ቡድን ከፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤልና ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ ጋር ቀጠናዊና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመቆጣጠር ላይ ትኩረት በማድረግ ውይይት አካሂደዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ከልኡክ ቡድኑ ጋር ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መንግስት ግንኙነት የጠበቀና በብዙ ዘርፎች በጋራ እየሰሩ የሚገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማትም ግንኙነታቸውን አዳብረው ሰላምና ደህንነትን በማስጠበቅ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን፣ ህገ ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውርን እንዲሁም በድንበር አካባቢ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በጋራ ለመቆጣጠርና የሚፈጠሩ ችግሮችንም በጋራ ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ቀደም ሲል ለደቡብ ሱዳን ፖሊስ መኮንኖች ይሰጥ የነበረው የዲፕሎማ መርሃ ግብር ስኮላርሺፕ በድግሪ መርሃ ግብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተፈቀደ መሆኑንና በቅርቡም የሱዳን ፖሊስ መኮንኖች ወደ ዩኒቨርስቲው እንደሚገቡ ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል።
በሌሎች የአቅም ግንባታ ስራዎችም ድጋፍ በማድረግ የሁለቱን ተቋማት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትኩረት እንደሚሰራም ነው የጠቀሱት።
የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ የፖሊስ አገልግሎት ኃላፊ ኢንስፔክተር ጀነራል ማጃክ አኬስ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ቤተሰባዊ አቀባበልና ፖሊስ ኮሚሽኑ እያደረገ ላለው ድጋፍ አክብሮት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ተቋማቱ የሁለቱን ሀገራት ጥብቅ ግንኙነት ወደ ፖሊስ በመውሰድ ቀጠናዊና አካባቢያዊ የደህንነት ስጋቶችን በመተንተንና የመረጃ ልውውጦችን በማድረግ ድንበር ዘለል የሽብርና ሌሎች ወንጀሎችን መከላከል እንደሚገባም ሃላፊው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ነፃነት ያበረከተችውን አስተዋፅኦ ምን ጊዜም እንደማይረሱትና በምንም መለኪያ ማንኛውም ሶስተኛ ወገን የኢትዮጵያንና የደቡብ ሱዳንን ግንኙነት ማበላሸት እንደማይችልም አረጋግጠዋል።
ግንኙነታቸው በደም የተሳሰረ መሆኑን በአፅንኦት የተናገሩት ኢንስፔክተር ጀነራሉ የኢትዮጵያ ህልውናና የደቡብ ሱዳን ጥቅም ለድርድር የማይቀርቡ ዋነኛ ጉዳዮች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ከውይይቱ በኋላ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ የፖሊስ ልኡክ ቡድን በኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤት የስራን አካባቢ ምቹ እና ተስማሚ ለማድረግ እየተካሄዱ ያሉ ግንባታዎችን ተዘዋውሮ በመጎብኘት ተሞክሮውን ወደ ሀገራቸው በመውሰድ እንደሚተገብሩም ገልፀዋል።