በወልድያ የፍተሻ ጣቢያ በቁጥጥር ስር የዋለው 161 ተቀጣጣይ ፈንጂ ጁንታው በአዲስ አበባና አካባቢው ለጥፋት ተልዕኮ ሊያውለው የነበረ ነው...የፈዴራል ፖሊስ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በወልድያ የፍተሻ ጣቢያ በቁጥጥር ስር የዋለው 161 ተቀጣጣይ ፈንጂ ጁንታው በአዲስ አበባና አካባቢው ለጥፋት ተልዕኮ ሊያውለው የነበረ ነው...የፈዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
አዲስ አበባ፣የካቲት 11/2013(ኢዜአ) የጁንታው የጥፋት ተልዕኮ በአዲስ አበባ እና አካባቢው ለመፈፀም አንድ መቶ ስልሳ አንድ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን የያዘ አይሱዙ መኪና ከነተጠርጣሪዎቹ በወልድያ የፍተሻ ጣቢያ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
ከትላንት በስቲያ ከቀኑ 11:00 ሰዓት ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘ የነበረ ኮድ 3 የሰሌዳ ቁጥር አ.አ. A21084 አይሱዙ የጭነት መኪና በቆራሊዮ እቃዎች ውስጥ አንድ መቶ ስልሳ አንድ ERA-EOI EX-RDX 01/2015/03 W/T-3.1 KG የተባሉ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን የጁንታው የጥፋት ተልዕኮ በአዲስ አበባ እና አካባቢው ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ በወልድያ ፍተሻ ጣቢያ በተሽከርካሪው ላይ ሙሉ ፍተሻ በማድረግ መያዙን ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንደገለጸው ተቀጣጣይ ፈንጂዎቹ ወደ መሀል ሀገር ቢገቡ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ ይችሉ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ የአሽከርካሪው ረዳት እንዲሁም የንብረቱን ባለቤቶች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል።
በፖሊስ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ /preliminary investigation/ ለማወቅ እንደተቻለው ሙሉቀን መስፍን በተባለ ሾፌር እና አንዱዓለም ዳንኤል በተባለ ረዳት ያሉበት አይሱዙ ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር የዋለው ጉዞውን የጀመረው ከደቡብ ክልል ሙዝ ጭኖ ሲሆን ሙዙን ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ አራግፎ ሲመለስ ፈንጂዎቹን ከቆራሊዮ ጋር ቀላቅሎ በመጫን የመልስ ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ እንደቀጠለ መያዙ ተገልጿል።
የንብረቱ ባለቤት ጡማይ ሹምዬ የተባለ በትግራይ ክልል የማይጨው ዞን የመሆኒ ወረዳ መሆኒ ቀበሌ 03 ነዋሪ ሲሆን ፖሊስ እንዳረጋገጠው በጁንታው ቡድን በጦርነት የተሳተፈና አሁን ተመሳስሎ በማምለጥ ተልዕኮ ወስዶ ሀገርን በሽብር ለማተራመስ ሲንቀሳቀስ እንደነበር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ተልዕኮውም የነበረው ከሌሎች የጥፋት ሀይሎች ጋር በመሆን ጥቃት ለማድረስ እንደነበር እንደተደረሰበት የገለጸው ኮሚሽኑ፤ በወንጀሉ ተባባሪነት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለው አማረ ተስፋዬ የተባለ የአላማጣ ነዋሪ የራሱን የንግድ ፍቃድ ለጡማይ አሳልፎ የሰጠ መሆኑም በተገኘው መረጃ መረጋገጡን ጠቁሟል።
የጁንታው ርዝራዦች አሁንም ሀገር የማፍረስ አጀንዳቸውን በመሀል ሀገር የሽብር ጥቃት በመፈፀም ለማሳካት ያደረጉት ሴራ ህብረተሰቡ የሰጠውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮንትሮባንድ ቁጥጥርና ክትትል ዳይሬክቶሬት አባላት እንዲሁም የጉምርክ ኮሚሽን ሰራተኞች ባደረጉት ፈጣን እንቅስቃሴ ማክሸፍ መቻሉን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በፍተሻ ጣቢያው ከአሁን በፊትም የተለያዩ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ተቀጣጣይ ቦምቦች እየተያዙ በመሆኑ የአካባቢው የፀጥታ ኃይል እና ህብረተሰቡ ተገቢውን ቅንጅት በማድረግ ለውጤት መብቃታቸውም ተገልጿል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የፀጥታና የህብረተሰብ ክፍሎች በቅርብ በመቀናጀት በየትኛውም ደረጃ የሚወጠኑ የሽብር ተግባራትን ለመቆጣጠር እንደተለመደው በጋራ እንዲሰሩ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
የምርመራው ውጤት የምርመራ ሂደቱ ሲጠናቀቅ በዝርዝር የሚያቀርብ መሆኑን ፌዴራል ፖሊስ ማምሻውን በላከው መግለጫ አመልክቷል።