ባህላዊ እሴቶቻችንን ለዘላቂ ጥቅም እንዲውሉ በትኩረት መሰራት አለበት- ዶክተር ሂሩት ካሳው - ኢዜአ አማርኛ
ባህላዊ እሴቶቻችንን ለዘላቂ ጥቅም እንዲውሉ በትኩረት መሰራት አለበት- ዶክተር ሂሩት ካሳው
ዲላ፣ የካቲት 11/2013( ኢዜአ) ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ በማልማት ዘላቂ ጥቅም እንዲያስገኙ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው አሳሰቡ።
የጌዴኦ ብሔር የዘመን መለወጫ የ"ዳራሮ" በዓል በዲላ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በበዓሉ ሥነ-ሥርዓት የተገኙት ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊ እሴት ባለቤት የሆነች የምስራቅ አፍሪካ ፈርጥ ሀገር ናት።
ሆኖም ባህላዊ እሴቶች በተገቢው መንገድ ጠብቆ ከማቆየት አንጻር ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል።
የጌዴኦ ዘመን መለወጫን ጨምሮ በዞኑ የሚገኙት የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሃብቶች ከእሴቶች ውስጥ እንደሚጠቀሱ የገለጹት ዶክተር ሂሩት "አጥንቶና አልምቶ ከመጠቀም አንጻር ከማህበረሰቡ በተለይም ከምሁራንና ከባለሃብቶች ብዙ ይጠበቃል" ብለዋል።
ባህላዊ እሴቶችን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ ታሪክ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመው ማህበረሰቡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ የራሳቸው ያልሆኑ መጤ ባህል ጋር እየተላመደ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀገሪቱን ህዝቦች ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር እንዲውሉ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለዚህም ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የጌዴኦ ህዝብ መልካ ምድር ከማልማቱም ባለፈ የአየር ንብረት ተጽዕኖን መቋቋም የሚችል አኩሪ የግብርና ባህል ባለቤት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ናቸው።
አኩሪ ባህላዊ እሴቶቻችን ቀደም ባለው ሥርዓት የተሳሳተ የፖለቲካ ትርክት የደበዘዘውን ወንድማማችነት ለመመለስ በሚያስችል መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ መስራት ይገባል ብለዋል።
የዘንድሮ የ"ዳራሮ" በዓል የፈጠረውን መነቃቃት በልማት ስራዎች ላይም መድገም ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጉዞ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በተለይ መጪው ምርጫ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የዜግነት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽፈራው ቦጋለ በበኩላቸው የዘንድሮ የ"ዳራሮ" በዓል ጌዴኦን ከወንድም ህዝቦች ጋር በፍቅር እንዳይኖር ሲያባላው የከረመው የህወሀት ጁንታ በለኮሰው እሳት በተቃጠለበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በበዓሉም አርቲስት ታማኝ በየነን ጨምሮ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ፣የጉጂ፣ ቦረና፣ ጌዴኦ አባ ገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የብሄሩ ተወላጆች ተሳትፈዋል።
የጌዴኦ ብሄር የዘመን መለወጫ በዓል የሆነውን "ዳራሮ " ምክንያት በማድረግ ከጉጂ፣ ቦረናና ጌዴኦ አባገዳዎች ለብሄሩ አባገዳ የተለያዩ የግብርና ምርቶች በስጦታ አበርክተዋል።