የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ስብስብ 'በአገሪቱ የተደረጉ ምርጫዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትና አፈና እንደነበረባቸው ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ስብስብ 'በአገሪቱ የተደረጉ ምርጫዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትና አፈና እንደነበረባቸው ገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11 ቀን 2013 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ያደረገቻቸው አምስት ምርጫዎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና አፈና የነበረባቸው ናቸው" ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ስብስብ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሰብዓዊ መብትን ያከበረና ሰብዓዊ መብትን አጀንዳው ያደረገ መሆን እንዳለበት አሳስቧል።
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት አዘጋጅነት የሲቪክ ማህበራትና የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ተወካዮች የታደሙበት ‘ምርጫና ሰብዓዊ መብት’ የተሰኘ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
'ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች' የተሰኘው የመብት ተሟጋች ድርጅት ኃላፊ አቶ ያሬድ ኃይለማርያም እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እስካሁን ያደረገቻቸው አገራዊ ምርጫዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትና አፈና የበረታባቸው ነበሩ።
ካለፉት አምስት ምርጫዎች በ1997 አንጻራዊ መሻሻል ቢታይም፤ ድህረ ምርጫ ፖለቲከኞች፣ ሲቪክ ማህበራትና ጋዜጠኞች ለጅምላ እስር፣ ግድያና ለአካላዊና ሥነ ልቡናዊ ጉዳት እንዲሁም ለስደት የተዳረጉበት እንደነበር አስታውሰዋል።
ከ1997 ምርጫ በኋላም መንግሥት ወደ አምባገነንነት የተለወጠበትና ሰብዓዊ መብቶች ያልተከበረባቸው ምርጫዎች እንደተካሄዱ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የተሻለ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ያሬድ፤ 6ኛው አገራዊ ምርጫም የቀደሙትን ምርጫዎች ስህተት አርሞ መካሄድ እንዳለበት ገልጸዋል።
"ለዚህም ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ሚዲያና ማህበረሰቡ ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው "ኮሚሽኑ 6ኛው አገራዊ ምርጫ የዜጎችን እኩል አሳታፊነት፣ ልዩ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ታሳቢ ማድረጉን ኮሚሽኑ ይከታተላል" ብለዋል።
በተጨማሪም ሰብዓዊ መብቶችን አጀንዳ ማድረግ እንደሚጠበቅ ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።
የፖለቲካ ድርጅቶች ቢመረጡ ድንጋጌዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ፤ የሰብዓዊ መብቶችን ጉዳይ የክርክርና የውይይት አጀንዳ ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።