የትግራይና የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት በኢንጂነር ስመኘው ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይና የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት በኢንጂነር ስመኘው ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ
መቀሌ/ጋምቤላ ሀምሌ 19/2010 የትግራይና የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ። የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኢንጂነሩ የኢትዮጵያ ህዳሴ እውን እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እያበረከቱ መቆየታቸውን በማውሳት ባጋጠማቸው ድንገተኛ ሞት የተሰማውን መሪር ሃዘን ገልጿል። ኢንጅነር ስመኝ አገሪቱ ካፈራቻቸው የልማት ሃዋሪያዎች መካከል አንዱ እንደነበሩ በመግለጫው አስታውቋል። በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በንቃትና በትጋት ተሰማርተው እየሰሩ ባለበት ወቅት ሞታቸው ሲሰማ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ከፍተኛ ድንጋጤና ሀዘን የተሰማው መሆኑንም በመግለጫው ጠቅሷል። ኢንጂነር ስመኘው ግዛው ለአገሪቱ የሕዳሴ ጉዞ እውን መሆን ላበረከቱት አስተዋፅኦ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ልዩ ክብርና አድናቆት ያለው መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል። መግለጫው አያይዞ እንደገለጸው የኢንጅነር ስመኘው ሞት ምክንያትን በተመለከተ የኢፊዲሪ መንግስት በአስቸኳይ አጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ የክልሉ መንግስት በላከው መግለጫ አስታውቋል ። የህዳሴ ግድቡ ግንባታን በበለጠ ፅናት፣ ወኔና ቆራጥነት ከፍፃሜው ለማድረስ የክልሉ መንግስትና ህዝብ እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም ዝግጁ መሆኑን በማረጋገጥ ለኢንጂነር ስመኘው ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና ጓደኞች መጽናናትን ተመኝቷል። የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ በበኩሉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል፡፡ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ኢትዮጵያ በዘመኑ ካፈራቻቸው ምርጥ ዜጎች አንዱ መሆናቸውን በመግለጫው አመልክተዋል። "ኢንጂነሩ ባላቸው እውቀትና ልምድ ለበርካታ ዘመናት ለኢትዮጵያ ህዝብ ቁጭትና ጥያቄ ሆኖ ለቆየው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን የዜግነት ግዴታቸውን ሲወጡ የነበሩ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነበሩ" ብሏል ፡፡ ኢትዮጵያ በእጅጉ የሚያስፈላጋትን ታላቅ ሰው በማጣቷ መላው የጋምቤላ ህዝብና የክልሉ መንግስት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ ለኢንጅነር ስመኘው በቀለ ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝቷል፡፡