ቀጥታ፡

ሸቀጦችን በመደበቅ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11 /2013 (ኢዜአ) የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ሸቀጦችን በመደበቅ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰበ።

ባለስልጣኑ በ2013 በጀት ዓመት የስድስት ወር አፈጻፀሙ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ መክሯል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሰለች ወዳጆ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ውድድር በሌለበትና የንግድ አሠራሮችን በተጣረሰ መልኩ የንግድ ተግባራትን የሚያከናውኑ አካላትን የመከላከል ስራ ሲሰራ ቆይቷል።

በአጥፊዎች ላይ ፍትሃዊ ውሳኔ በመስጠትም የሸማቹና የንግዱን ማህበረሰብ መብት ለማስጠበቅ መሞከሩንም ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ ይህንን ስራ ቢሰራም የሸማቹንና የንግዱን ማህበረሰብ እርካታ ለማረጋገጥ በርካታ ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ሆን ብለው ሸቀጦችን በመደበቅ እና በተለያየ መንገድ የንግዱ ስርዓት እንዲዛባ የሚያደርጉ አካላት አሉ።

ምርቶችን ደብቆ በማከማቸት፣ ያለአግባብ ዋጋ በመጨመርና በማናር ህብረተሰቡ እንዲጨነቅ የሚያደርጉ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ሸማቹ ማህበረሰብም ገበያውን አስተውሎ እንዲሸምትና ወቅትን ተከትሎ እጥረት የሚከሰትባቸው ምርቶች ሲኖሩ ግብይቱን በመተሳሰብ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

ሸማቹ በገበያው ያለአግባብ የዋጋ መናር ሲያስተውል ለባለስልጣኑ በአካልም ሆነ በስልክ ጥቆማ መስጠት እንደሚችል አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበር መስራችና አስተባባሪ ሻምበል ገብረመድህን ቢረጋ በበኩላቸው ሸማቹ ማህበረሰብ መብቱን ሊያስከብር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የህዝብን ታጋሽነት እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በሸማቹ ማህበረሰብ ላይ ጫና የሚፈጥሩ ነጋዴዎች ላይ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

መንግስት እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ ጠያቂና ለመብቱ የሚቆም ሸማች እንዲፈጠር መስራት እንዳለበትም አመልክተዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም