የምስራቅ አፍሪካ የጋራ ልማት - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ የጋራ ልማት
ገዛኸኝ ደገፉ /ኢዜአ/
ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ችግር እንደሚታይባቸው ዓለም አቀፍ ጥናቶች ያመለክታሉ። ከግብጽ በስተቀር አብዛኛዎቹ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የኤሌክትሪክ ሃይል ሽፋን በአማካይ ከ40 በመቶ አይበልጥም። ይህ ደግሞ ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ማነቆ ከመሆኑም ባሻገር በጤና፣ በትምህርት እና በአጠቃላይ የኑሮ ዘይቤ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በእናቶችና ህፃናት ሞት ምጣኔ ከፍተኛ ድርሻ ይወስዳሉ። የትምህርት ተደራሽነትም ዝቅተኛ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከዓለማችን ደሃ ሀገራት መካከልም የምስራቅ አፍሪካ ተጠቃሽ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት በተጨማሪ በማህበራዊው ዘርፍ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የተለያዩ ጥናታዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። ግድቡ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን እንዲሁም የተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለማስፋፋት እንደሚያስችልና ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ይጠቁማሉ።
ዘ ኮንቨርዜሽን የተሰኘው ድረ ገጽ “The Grand Ethiopian Renaissance Dam is the new reality” በሚል ርእስ ባስነበበው ጽሑፉ ላይ ኢትዮጵያ ለናይል ተፋሰስ 85 በመቶ ውሃ የምታበረክት መሆኑን አመልክቶ አስራ አንዱ የተፋሰሱ ሀገራት ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይገልጻል። የተፋሰሱ ሀገራት የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽነታቸውን ማስፋት ከቻሉ በትምህርትና በጤና ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ይዘረዝራል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አዳዲስ ተስፋዎችን ይዞ እንደሚመጣም ጽሑፉ አስነብቧል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋነኛ ዓላማ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ሲሆን፤ ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 6000 ሜጋ ዋት ሃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም የሀገሪቱን የሃይል ፍላጎት ከማሟላት አልፎ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ተጠቃሚ ያደርጋል።
የግድቡ መገንባት ለታችኞቹ የዐባይ ተፋሰስ ሀገራት ማለትም ለሱዳን እና ግብጽ ተጨማሪ ጥቅም እንደሚሰጥ ጥናቶች ያሳያሉ። University of Huddersfield Repository የህዳሴው ግድብ ለግብጽ እና ሱዳን የሚሰጠውን ጠቀሜታ አስመልክቶ ይፋ ባደረገው ጥናት ሁለቱ ሀገራት በጎርፍ ከመጥለቅለቅ አደጋ እንደሚታደጋቸው አመልክቷል። በተጨማሪም የውሃ ፍሰቱን ጠብቆ እንዲሄድ በማድረግ ድርቅን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጿል። ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን እንዲሁም የናይል ተፋሰስ ሀገራት በጋራ ለመበልጸግ፣ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣትና ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ እንዲሁም የሚያጋጥሟቸውን ማናቸውም ችግሮች በቀላሉ ለመፍታት ብቸኛው መንገድ በትብብር መስራት መሆኑንም ይጠቁማል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለናይል ተፋሰስ ሀገራት የሚሰጠው ጠቀሜታ እጅግ የጎላ ስለመሆኑ ብዙዎች የመሰከሩለት እውነታ ቢሆንም የአባይ ወንዝ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ሱዳን እና ግብጽ ግን ዓመታትን የፈጀ ውዝግብና ክርክር ሲያደርጉ ቆይተዋል። በኢትዮጵያ፣ በግብጽ እና ሱዳን መካከል የግድቡ ግንባታ መጀመርን ተከትሎ በርካታ ጊዜያቶች የሶስትዮሽ ድርድሮች ቢደረጉም ይህ ነው የሚባል ስምምነት ላይ ሊደርሱ አልቻሉም። በየጊዜው በሚካሄዱ ድርድሮች ግብጽ በምታራምደው ግትር አቋም ዋነኛ ተዋናይ መሆኗ የሚታወቅ ቢሆንም አንድ ጊዜ ሱዳን ሌላ ጊዜ ደግሞ ግብጽ ከድርድሩ ሃሳብ በማፈንገጥ መፍትሔ ላይ መድረስ ሳይቻል ቀርቷል።
በቅርቡ የተካሄዱ መድረኮችን እንኳ ለማሳያነት ብንወስድ የኢትዮጵያ የዉኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ታህሳስ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት በበይነ-መረብ ስብሰባ አካሂደዋል። የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሰየሟቸው ባለሙያዎች ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድ ኢትዮጵያ በበጎ እንደምትመለከተው-- የሱዳን ወገንም ሰነዱ ጠቃሚ አድርጎ እንደሚመለከተው የግብጽ ወገን ግን ሰነዱን ጨርሶ እንደማይቀበለው አሳውቋል።” በማለት ውይይቱ ያለስምምነት መጠናቀቁን ገልጿል። ከዚህ መድረክ በኋላ ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው ስብሰባ ደግሞ አገራቱ ከአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ጋር ስብሰባ መካሄዱን ተከትሎ ውጤቱ ለሕብረቱ ምክር ቤት ሊቀመንበር እንዲቀርብ በሚለው ሃሳብ ላይ ኢትዮጵያና ግብጽ ሲስማሙ ሱዳን እንዳልተቀበለችው በወቅቱ የወጣው መግለጫ አመላክቷል።
የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ አሜን ጋሻው በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ባቀረቡት ትንታኔ ኢትዮጵያ በርካታ ሚሊዮን ዜጎቿን ከድህነት ለማውጣት በማሰብ እያስገነባችው ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ፤ ግብጽ የወንዙ ብቸኛ ተጠቃሚነቷን ያሳጣኛል በማለት ፕሮጀክቱን በአዎንታ ከማየት ይልቅ ለማደናቀፍ የተለያዩ አካሄዶችን እንደምትከተል አመልክተዋል። የአባይ ውሃ አጠቃቀምን በሚመለከት ከግብጽ ጋር የተደረጉ ንግግሮች ሁሉ በግብጽ ግትርነት ምክንያት ይሄ ነው የሚባል ውጤት ሳያመጡ መቅረታቸውን በማስታወስ፤ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተደረጉ ጥረቶችን ዋጋ በማሳጣትና አላስፈላጊ ንትርክ እየፈጠረች ዛሬ ላይ መድረሷን አስገንዝበዋል።
ተመራማሪው አሜን ጋሻው እንደሚገልጹት የህዳሴው ግድብ ከኢትዮጵያም ሆነ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አልፎ ለመላው አፍሪካ ልማትና ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በዚህም ግድቡ የአፍሪካ ህዳሴ ምልክት ነው ሲሉ ይገልጹታል። የአፍሪካ ሃገራትም ልዩነቶቻቸውን አቻችለው ለጋራ ጥቅማቸው በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል በማለት ምክራቸውን ለግሰዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ አገልግሎት ላይ ሲውል የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደመሆኑ መጠን ፋይዳውን አሻግሮ በመመልከት ግንባታው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ሀገራቱ በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል። በግድቡ ዙሪያ የሚነሱ አወዛጋቢ ጉዳዮችንም ለመፍታት በሚያስችሉ አቅጣጫዎች ዙሪያ ተቀራርበው መነጋገር ይኖርባቸዋል። የህዳሴው ግድብ ለናይል ተፋሰስ ሀገራት በጋራ የመልማት እድል የሚሰጥ ሀብት እንጂ የልዩነት መንስኤ የሚሆን አይደለም። የተፋሰሱ ሀገራት በመሰረተ ልማት፣ በንግድ፣ በትምህርትና ጤና፣ በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በሌሎችም መስኮች የሁለትዮሽና የባለብዙ ዘርፍ ግንኙነቶችን ቢያጠናክሩ ግድቡ ከድህነት ለመላቀቅ ለሚያደርጉት ትግል ተደማሪ አቅም እንደሚፈጥርላቸው በመገንዘብ ለጋራ ልማት አብሮ የመስራት ባህል ማዳበር ይገባቸዋል እንላለን።