ቀጥታ፡

በዘንድሮ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመራጩን ነጻነት ሊያከብሩ ይገባል..የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች

ሚዛን፣ የካቲት 11/2013 (ኢዜአ) በዘንድሮው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ በማድረግ የመራጩን ነጻነት ሊያከብሩ እንደሚገባ በቤንች ሸኮ ዞን የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በዘንድሮ ምርጫ ለመወዳደር በአካባቢው የሚንቀሳቀቁ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምርጫው ሰላማዊና ፍትሀዊ እንዲሆን ለአባላት ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ ችግሮችን በጋራ ምክር ቤት ለመፍታት አቅጣጫ ይዘው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።


ምርጫውን አስመልክተው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች እንዳስታወቁት ሀገሪቱ በሀሳብ የበላይነት የሚያምኑና ሀገራዊ አንድነት ላይ ልዩነት የሌላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጓታል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ታጠቅ ከበደ እንዳሉት በዘንድሮው ምርጫ ለህዝብ ጥቅምና መብት መከበር ተግቶ የሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።

ምርጫው ነጻና ፍትሀዊ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት አቶ ታጠቅ "ምርጫው ፍትሀዊና ነጻ እንዲሆን መራጩ ያለማንም ጫናና ጉትጎታ እንዲሳተፍ ነጻነቱ ሊጠበቅ ይገባል" ብለዋል።

ወይዘሮ ሜሮን ታመነ በበኩላቸው ማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን ለህዝብ ከማስተዋወቅ ባለፈ አላስፈላጊና አወዛጋቢ ሃሳብ ከማሰራጨት ሊቆጠቡ እንደሚገባ አመላክተዋል።

"የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግና ደንብ አክብረው መንቀሳቀሳቸው ለመራጮች ምቹ መደላድል እንዲፈጠርና ምርጫው ካለምንም እንከን በሰላም እንዲካሄድ ያስችላል" ብለዋል።

"የፖለቲካ ፓርቲዎች በኃላፊነት መንፈስ በመንቀሳቀስ ምርጫው ግልጽና ፍትሃዊ ሆኖ በሰላም እንዲጠናቀቅ መስራት ይጠበቅባቸዋል" ያሉት ደግሞ አቶ ዘላለም ልክያለው ናቸው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቅድመ እስከ ድህረ ምርጫ ባለው ሂደት የዜጎችን መብትና ነጻነት አክብረው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አቶ ዘላለም አመልክተዋል።


በዘንድሮው 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ለመወዳደር በአካባቢው እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ የቤንች ሸኮና ምዕራብ ኦሞ ዞን ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደነቀ ደሳለኝ በቅድመ ምርጫ ዝግጅት ሰራ እስካሁን የፓርቲው ፕሮግራምና ማኑፌሰቶ መሰራጨቱን ገልፀዋል።

በምርጫው ሂደት ደግሞ ሃገራዊ አመለካከትና ሃሳብ በመሸጥ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቅሰው በሂደቱ የሚያጋጥም ችግርን በጋራ የፓርቲዎች ምክር ቤት እየፈቱ ለመሄድ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኩርታ በበኩላቸው በሁሉም የምርጫ ክልሎች ለክልልና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ እጩዎችን በህዝብ ለማስተቸት ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አላስፈላጊ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ለፓርቲው አባላት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ምርጫው አሳታፊና ሰላማዊ እንዲሆን ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና በየደረጃው ከሚገኙ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም