ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የአድዋ መታሰቢያ ፓርክ መሰየሙ ትውልዱ የአባቶቹን የድል ታሪክ እንዲገነዘብ ያግዛል -ዶክተር ሂሩት ካሳው

ጋምቤላ፣ የካቲት 11/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የአድዋ መታሰቢያ ፓርክ መሰየሙ የአሁኑ ትውልዱ የአባቶቹን አንድነትና ድል አድራጊነት ታሪክ እንዲገነዘብ የሚያግዝ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ገለጹ።

ሚኒስትሯ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በጋምቤላ ከተማ የተሰየመውን የአድዋ መታሰቢያ ፓርክና ሌሎች ታሪካዊ ሥፍራዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ሚኒስትሯ እንዳሉት በክልሉ ማዕከል የአድዋ መታሰቢያ ፓርክ መሰየሙ የአሁኑም ሆነ ቀጣዩ ትውልድ ስለአባቶቹ አንድነትና አይበገሬነት በመገንዘብ ሀገሩን የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ያግዛል።

ትውልዱ የአድዋ ድል ታሪክ ቅብብሎሽን የሚያጠናክር ጭምር መሆኑም ተናግረዋል።

ጋምቤላ ከተማ ሰፊ ያልተነገረላቸው ቅርሶች ባለቤት መሆኗን በመስክ ጉብኝታቸው ማረጋገጥ መቻለቸውን ጠቁመው ቅርሶቹ ተጠብቀውና ለምተው ለትውለዱ እንዲተላለፉ መስራት ይገባል ብለዋል።

ሚኒስትሯ የክልሉ መንግስት በጋምቤላ ከተማ የአድዋ መታሰቢያ ፓርክ በመሰየም ታሪኩ እንዲታወስ ላደረገው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ አጁሉ በበኩላቸው ፓርኩን መሰየም ያስፈለገው አድዋ የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ህዝቦች የድል ቀን በመሆኑ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በአባቶች አንድነትና አይበገሬነት በአድዋ የተገኘውን የድል ገድል ትውልዱ እንዲገነዘበውና እንዲያስታውሰው በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል።

በጋምቤላ ከተማ ቀበሌ አንድ ቤተ መንግስት አካባቢ ለአድዋ ድል መታሰቢያነት የተሰየመው ፓርክ ከሶስት ሺህ ካሬ በላይ ስፋት እንዳለው የገለጹት ደግሞ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ ናቸው።

የመታሰቢያ ፓርኩ የተለያዩ ዲዛይኖች ተዘጋጅተውለት ለከተማው ውበት በሚሆን መልኩ አረንጓዴና ጽዱ ለማድረግ ቢሮው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቅንጅት ለማልማት አቅዷል ብለዋል።

ሚኒስትሯ ከክልል የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በኢጣሊያ ወረራ ወቅት የኢትዮጵያ ወዳጆች አጋርነታቸው ለማሳየት ተዋግተው የተሰው የውጪ ሀገር ዜጎች መካነ መቃብር ጨምሮ የተለያዩ ታሪካዊ ሥፍራዎችን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም