የጥርብ ድንጋይ ንጣፍ ሥራ በመጓተቱ ለችግር ተዳርገናል-የቆሼ አካባቢ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የጥርብ ድንጋይ ንጣፍ ሥራ በመጓተቱ ለችግር ተዳርገናል-የቆሼ አካባቢ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ ሀምሌ 19/2010 በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለጥርብ ድንጋይ ንጣፍ (ኮብል ስቶን) ተብሎ የተቆፈረ መንገድ በመጓተቱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ችግር እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ። በአዲስ አበባ በተለያየ አካባቢዎች የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የጥርብ ድንጋይ ንጣፍ (ኮብል ስቶን) ሥራ እየተካሄደ ነው። የኢዜአ ሪፖርተር በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ተዘዋውራ ባደረገችው ቅኝት ለመንገድ ስራ ተብሎ የሚካሄድ ቁፋሮ በኅብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ እየፈጠረ ነው። ቆሼ ኔትዎርክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን መንገድ በጥርብ ድንጋይ ንጣፍ ለመሥራት ከተቆፈረ ከአንድ ወር በላይ መሆኑን የሚገልጹት ነዋሪዎቹ ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ የሚመጣ ጎርፍ እንቅስቃሴያቸውን እያወከ እንደሆነ ተናግረዋል። ለመንገዱ የዲች ማሰሪያ የሚውል በአጠቃላይ 600 ሺህ የሚሆን ብር ከአካባቢው ህብረተሰብ መሰብሰቡን የልማት ኮሚቴው ገልጿል። ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጎርፍ ወደ መኖሪያ ቤታቸው እየገባ እንደሆነ የገለጹት ነዋሪዎቹ መንገዱ በጭቃ የተበላሸ በመሆኑ ህጻናት፣ አዛውንቶች፣ ነፍሰ ጡር እናቶችና አካል ጉዳተኞች ወጥተው ለመግባት እንደተቸገሩም ተናግረዋል። የአካባቢው የሙላት ማህበር የልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደምለው ስጦታው እንደተናገሩት ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ የሚመጣ ጎርፍ ችግር ነዋሪዎቹ ላይ እየተፈጠረ ሲሆን በተደጋጋሚ ፍሳሹ አንዲወገድ ለወረዳም ለክፍል ከተማም ጥያቄ እያቀረቡ ቢሆንም አፋጣኝ መልስ አለመገኘቱንና ችግሩ አልመቀረፉን ተናግረዋል፡፡ የሚመጣው ውሃ እንዳለ ቤታቸው እንደሚገባና ልጆቻቸውን ተሸክመው ለመውጣት መገደዳቸውንና ችግሩ ለህይወታቸው በጣም አስጊ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ ሃያት ጃፈር ናቸው "ውሃው እንዳለ መጥቶ እኔ ላይ ነው የሚንጣለለው፡፡ ቤቴ በስብሷል ሊወድቅ የተጋደመ ነው እኔም ሆንኩኝ ጎረቤቶቹ አንድ አይነት ኑሮ ነው የምንኖረው፡፡ አፈር በመሸከም ከነባለቤቴና ልጆቼ በሽተኛ ሆነናል፡፡ ይኽው አፈር በማዳበሪያ እያጋዝን ነው ያለነው ዝናብ ሲያጉረመርም ሃሳባችን ለምንበላው፣ ለምንጠጣው፣ ለምንለብሰው ሳይሆን ከአሁን አሁን ገባብን የት እንውደቅ ወዴት ነው የምንሰደደው።" ያሉት ደግሞ አቶ እጅጉ አዳነ ናቸው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ 2 የህብረተሰብ ተሳትፎ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ተስፋዬ በበኩላቸው የችግሩ መንስዔ በአካባቢው በሚካሄድ የውሃ ፍሳሽ ማስወገጃ ምክንያት በመሆኑ ሥራው ለአንድ ወር ያህል መቋረጡን ገልጸዋል። በአካባቢው ያለውን ችግር ለመፍታት ኮረት ድንጋይ የማልበስ ሥራ የሚሰራ ሲሆን ክረምቱ ሲወጣ የጥርብ ድንጋይ የማንጠፍ ሥራ የሚከናወን መሆኑን ጠቁመዋል።