ዘመናዊ የስራ አፈፃፀም መቆጣጠሪያ ስርዓት ለማበልፀግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
ዘመናዊ የስራ አፈፃፀም መቆጣጠሪያ ስርዓት ለማበልፀግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የመድሃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ ዘመናዊ የስራ አፈፃፀም መቆጣጠሪያ ስርዓት በጋራ ለማበልፀግ የሚያስችላቸውን የኮንትራት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ኤጀንሲው ዘመናዊ የስራ መከታተያ መተግበሪያውን በመጠቀም በዓመት 378 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ማዳን ያስችለዋል ተብሏል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ጋልጋሎ ለኢዜአ እንዳሉት ኤጀንሲው ጠንካራ የስራ ባህልን ለማዳበር የቁጥጥር እና ክትትል ስርዓቱን እያዘመነ ነው፡፡
ኤጀንሲው የ10 ዓመት የመድሀኒት አቅርቦት እቅዱን መተግበር የጀመረ ሲሆን እቅዱን ተፈፃሚ የሚያደርግበት የተለያዩ ስትራቴጂዎች በመንደፍ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
የሰራተኞችን የስራ ላይ ቅልጥፍና እና የስራ አፈፃፀም በዘመናዊ መልኩ መከታተል በ10 ዓመት የልማት እቅዱ አተገባበር ውስጥ ከተነደፉ አሰራሮች መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡
ይህ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት የሚበለፅገው ዘመናዊ የሰራተኞች መቆጣጠሪያ መተግበሪያ ለአጠቃቀም ቀላል እና ምቹ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም የኤጀንሲው ሰራተኞች የትም ቦታ ሆነው ስልካቸውን በመጠቀም በቀላሉ የሚገለገሉበት ነው ተብሏል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት መተግበሪያው የግል አፈጻጸምን መከታተያና የስራ መቆጣጠሪያ መያዙ በተቋሙ ግልፅ አሰራር በማስፈን ሰራተኞች ራሳቸውን እንዲመለከቱ ያደርጋቸዋል፡፡
የሰራተኞች የስራ አፈፃፀም መከታተያ ስርዓት ግልፅ የሆነ የግልና የቡድን አሰራርን በተቋሙ ውስጥ የሚያሰፍን ነው ተብሏል፡፡
መተግበሪያው ከተቋሙ መቋቋሚያ አዋጅ ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ እንደሚበለጽግም ተገልጿል፡፡
ስርዓቱ ተግባራዊ ሲደረግ የኤጀንሲውን ሰራተኞች የስራ አፈጻጸም ዘመናዊ በሆነ መንገድ መገምገም ያስችላል ተብሏል፡፡