ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት የተሻለ ትብብር ይፈጥራል-ትውልደ ኤርትራዊያን

አዲስ አበባ ኀምሌ 19/2010 በቅርቡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረገውን የሠላም ስምምነት ተከትሎ ሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ የትብብር ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር ወጣት ትውልደ ኤርትራዊያን ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሃያ ዓመታት የቆየውን አለመግባባት በመቋጨት የደረሱበት የሰላም ስምምነት እምነት የሚጣልበት ነው ብለዋል። ወጣት ትውልደ ኤርትራዊያን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ሁለቱ መሪዎች በአገራቱ መካከል የነበረውን የጦርነት ምዕራፍ ለመዝጋት በአስመራ የሰላም ስምምነት ሲፈራረሙ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል። በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሃያ ዓመት በኋላ ወደ አስመራ የቀጥታ በረራ ሲጀምር ተጓዥ የነበረችው ወጣት ያቤላ መሃሪ አንዷ ናት። የቀጥታ በረራው ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ መጀመሩ በአገራቱ ግንኙነት ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና በቀጣይ ለሚኖራቸው የትብብር መስክ ብሩህ ተስፋ የሚሰንቅ ነው ብላለች። ወጣት ያቤላ እንዳለችው "የሰላም ስምምነቱ ለኤርትራና ለኢትዮጵያኖች ተስፋና ዳግም ለመገናኘት መነሳሳትን የሚሰጥ ክስተት ነው።" የክረምት ወቅትን ምክንያት በማድረግ ለእረፍት ከለንደን ወደ አስመራ የመጣው ወጣት ፍጹም ሃዲጉ በበኩሉ ኢትዮጵያና ኤርትራ ለሃያ ዓመታት ከነበሩበት አለመግባባት ወጥተው አዲስ ምዕራፍ ለሕዝቦቻቸው አውጀዋል ብሏል። በስዊድን የምትኖረው ወጣት ልዋህም ህሩይ እንዳለችው አገራቱ የድንበር ውዝግባቸውን ይፋዊ በሆነ መልኩ ለማቆም መስማማታቸው እንዳስደሰታት ገልጻለች። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተደረሰው የሠላም ስምምነት ለአገራቱ ሕዝቦች ትልቅ ትርጉም አለው ያለው ደግሞ በዋሸንግተን ነዋሪ የሆነውና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የመጣው ወጣት አማን ዮሃንስ ነው። በተመሳሳይ በኖርዌይ የሚኖረው ወጣት አሌክሳንደር ኤፍሬም እሱና ጓደኞቹ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሠላም ከሆኑ አዲስ አበባን ለመጎብኘት እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም