ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ጥሪ የተደረገላቸው የፋሲል ከነማ ተጨዋቾች ቡድኑን አልተቀላቀሉም - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ጥሪ የተደረገላቸው የፋሲል ከነማ ተጨዋቾች ቡድኑን አልተቀላቀሉም
በካሜሮን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ጥሪ የተደረገላቸው የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች ቡድኑን አለመቀላቀላቸውን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ገለፀ።
አሰልጣኝ ውበቱ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ ለብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት 28 ተጫዋቾች ተጠርተው 24 ተጫዋቾች ብቻ ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጿል።
በብሔራዊ ቡድኑ የሁለተኛ ዙር ልምምድ ያልተገኙት የፋሲል ከነማ ተጫዋቾቹ ያሬድ ባዬ፣ አምሳሉ ጥላሁን፣ ሀብታሙ ተከስተ እና ሺመክት ጉግሳ መሆናቸውን አሰልጣኙ ይፋ አድርጓል።
የማጣሪያ ጨዋታዎቹ በመጋቢት የሚካሄዱ በመሆናቸው ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ቡድኑን እስኪቀላቀሉ እንደሚጠበቁ ገልጿል።
የሁለተኛው ዙር የብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ከኮትዲቯርና ከማደጋስካር ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ያለውን ጨዋታ መሰረት ያደረገ ነው ያለው አሰልጣኙ ቡድኑ ልምምድ ከጀመረ 6 ቀናት ማስቆጠሩን ገልጿል።
በልምምዱ ተጫዋቾቹ ያሳዩት ተነሳሽነት ከፍተኛና ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ይህም የብሔራዊ ቡድኑን ለቀጣይ ጨዋታዎች መስመር ለማስያዝ ይረዳል ብሏል።
ክለቦች እረፍት ላይ በመሆናቸው ግን የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማድረግ አለመቻሉንና ያም ቢሆን አጠቃላይ ዝግጅቱ በመልካም ሁኔታ እየሄደ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የፋሲል ከነማ ክለብ "ተጫዋቾቼ ድካም ስላለባቸውና ክለቡ ለሻምፒዮንነት ስለሚፎካከር" ተጫዋቾቹን አልላኩም ብሏል።
በተጨማሪም በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ሕግ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድን የሚቀላቀሉት ጨዋታው 15 ቀን ሲቀረው እንደሆነና ጨዋታው የሚደረገው ከአንድ ወር በኋላ በመሆኑ ተጫዋቾቹን ያለመልቀቅ መብት እንዳለው አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በካሜሮን አስተናጋጅነት በ2014 ዓ.ም የሚዘጋጀው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 11 እስካሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ስድስት ነጥብ በመሰብሰብ ኮትዲቯርና ማደጋስካርን ተከትሎ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ኮትዲቯር በስምንት ነጥብ፣ ማደጋስካር በሰባት ነጥብ በምድቡ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ዋልያዎቹ ከኮትዲቯርና ከማደጋስካር ጋር ቀሪ የማጣሪያ ጨዋታቸውን በመጋቢት 2013 ያደርጋሉ።