የአሁኑ ትውልድ የድሉን ታሪክ በመጠበቅ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሊሰራ ይገባል-ዶክተር ሂሩት ካሳው - ኢዜአ አማርኛ
የአሁኑ ትውልድ የድሉን ታሪክ በመጠበቅ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሊሰራ ይገባል-ዶክተር ሂሩት ካሳው
ጋምቤላ ፤ የካቲት 10/2013 (ኢዜአ) የአሁኑ ትውልድ ጀግኖች አባቶች በአድዋ ያስመዘገቡትን የድል ታሪክ በመጠበቅ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ተናገሩ ።
’’አድዋ የህብረ-ብሔራዊ አንድነት አርማ’’በሚል መሪ ሃሳብ 125ኛ የአድዋ በዓል በክልል ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል።
በክብረ በዓሉ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት ሚኒስትሯ እንዳሉት ጀግኖች አባቶችና እናቶች ለህይወታቸው ሳይሳሱ የውጭ ወራሪን አሳፍረው በመመለስ ነፃነቷ ያልተደፈረ ሀገር ለትውልድ ትተው አልፈዋል።
የአድዋ የድል ታሪክ ዛሬም ድረስ መላው ጥቁር ህዝቦች ዘንድ የነፃነት ተምሳሌ ተደርጎ የሚቆጠርና ኢትዮጵያዊያን አንገታቸውን ቀና አድረገው እንዲጓዙ ያደረገ አኩሪ ገድል ነው ብለዋል።
ቀደምት አባቶችና እናቶች በአድዋ የገጠማቸውን ፈተና በድል አድራጊነት በማለፍ ነፃነቷ የተጠበቀ ሀገር እንዳወረሱ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ከድህነት ታላቃ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አባቶች በአድዋ አኩሪ ድል የተጎናጸፉት ብዙ ሆነው አንድ የመሆናቸው ሚስጥር ነው ያሉት ሚኒስትሯ የዘመኑ ትውልድም አንድነቱን በማጠናከር የኢትዮጵያን እድገት ለማፋጠን አበክሮ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተለይም የአሁኑ ትውልድ የሚታወሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሆኑን ጠቅሰው በሌሎች የልማት ስራዎችም በንቃት በመሳተፍ ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ በአንድነት ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሚኒስትሯ የአድዋ በዓል በአማረና ደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ላደረገው የጋምቤላ ክልልን አመስግነዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ አጁሉ በበኩላቸው የአድዋ ደል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማህተምና የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ዓርማ መሆኑን ተናግረዋል።
አድዋ የአውሮፓ ወራሪዎች ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን በቀኝ ግዛት ለመቀራመት የነበራቸው እሳቤ የሰበረ ታላቅ የድል ታሪክ መሆኑን ገልጸዋል።
ጀግኖች አባቶች የውጭ ወራሪዎች አሳፍረው የመመለሳቸው ስኬት ዘር ፣ቀለምና ሃይማኖት ሳይለያቸው በአንድነትና በአይበገሬነት የመታገላቸው ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።
የዘመኑ ትውልድ ከአባቶቹ የድል ታሪክ በመማር በሀገር ላይ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በአንድነት ታግሎ የማለፍ እሴቱን ሊያጎለብት ይገባል ብለዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነት መገለጫ አርማ በሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚፈጠሩ ጫናዎችን በመመከት ለግድቡ ግንባታ እውን መሆንና ለሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ ስኬት የአሁኑ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
የአድዋ ድል ሁሉም ኢትዮጵዊያን ያለ ምንም ልዩነት በአንድነት የውጪ ወራሪን አሳፍረው የመለሱበት ታላቅ ታሪካዊ በዓል መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዴች ቦል ናቸው።
የአድዋ በዓል በክልል ደረጃ በጋምቤላ ከተማ በፓናል ውይይት፣በስፖርት ውድድርና ሌሎች ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሮ ውሏል።