ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ህንድ በኢትዮጵያ የምታካሂደውን የኢንቨሰትመንት ተሳትፎ እንድታጠናክር ጠየቁ

የካቲት 10 / 2013 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ህንድ በኢትዮጵያ የምታካሂደውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንድታጠናክር ጠየቁ።

የኢትዮ-ህንድ ቢዝነስ ፎረም በህንድ በመካሄድ ላይ ነው።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ልዑክ በህንድ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረገ ሲሆንል ልዑኩ የኢትዮ-ህንድ ቢዝነስ ፎረም ላይም ተሳትፏል።

በዚህ ወቅት አቶ ደመቀ የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በስራ እድል ፈጠራና ኢኮኖሚውን በመደገፍ ረገድ ትልቅ እገዛ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሁለቱ አገሮች ባላቸው የንግድ ግንኙነት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚገመት ሀብት መፈጠሩን አመልክተው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚገኙ 30 የህንድ ኩባንያዎች ላሳዩት ጥንካሬ ምስጋና አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የ10 አመት የኢኮኖሚ ልማት ዕቅድ በማዘጋጀት በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሳይንስና በሌሎችም ዘርፎች በአፍሪካ ረገድ ብልጽግናን በማሳካት ምሳሌ ለመሆን እየሰራች መሆኑ አስታውቀዋል።

ለዚህም በቂ የሰው ሃይል፣ የኢኮኖሚ ማበረታቻዎች፣ ለኢንቨስተሮች አስተማማኝ ዋስትና የሚሆን መንገዶችን መዘርጋቱንና ለሙስና የሚሆን ምንም አይነት ክፍተት እንደማይተው አቶ ደመቀ ገልጸዋል።

ህንድም በኢትዮጵያ ምታካሂደውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ቁጥር በመጨመር አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮ-ህንድ ቢዝነስ ፎረም በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲና በህንድ የንግድ ምክር ቤት የተዘጋጀ መሆኑን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም