ቀጥታ፡

በቅዱስ ያሬድ ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥነው ዘጋቢ ፊልም እሁድ ይመረቃል

የካቲት 9/2013 (ኢዜአ) የቅዱስ ያሬድን ታሪክና ሥራዎች የያዘ ዘጋቢ ፊልም የካቲት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ይመረቃል።የደብረሐዌ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ኮሚቴ የቅዱስ ያሬድን ዘጋቢ ፊልም አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ሶስት ዓመት የፈጀዉ የቅዱስ ያሬድ ዘጋቢ ፊልም 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፤ የ1 ሰዓት ከ6 ደቂቃ ርዝማኔ አለው።

የአሀዱ ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ እንደገለጸው፤ ዘጋቢ ፊልሙን መስራት ያስፈለገዉ ቅዱስ ያሬድን አስመልክቶ በርካታ ጥናቶችና ምርምሮች ቢደረጉም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልቶ የወጣ የማስተዋወቅ ሥራ ባለመሰራቱ ነው።

በጎንደር ከተማ ልዩ ቦታዉ “ፀለምት” በሚባለዉ ሥፍራ የሚገኘዉ የቅዱስ ያሬድ ገዳም በሚገኝበት ቦታ ስለያሬድ ሥራዎች ጥናትና ምርምር የሚደረግበት ማዕከል ለመክፈት በኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር ገዳሙ መሠረታዊ ይዘቱን ሳይቀይር ግንባታ ለማካሄድ ጥናት እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዘጋቢ ፊልሙ የቅዱስ ያሬድን ስራዎች በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ዓላማ እንዲውል እንደሚደረግም ጋዜጠኛ ጥበቡ ገልጿል።

የጉባኤ ኪን ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ልጅ ወንድሜ ላዕከማርያም በበኩሉ የቅዱስ ያሬድ አስተምህሮ በድርሰት፣ በዜማ፣ በዝማሬ፣ በቅኔና በሥነመለኮት ዙሪያ ብቻ ሳይሆን ለሥነልቦናና ለሥነምግባር አስተዋፅኦ እንዳደረገም ገልጿል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዉጪ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ቤተክርስቲያኗ የያሬድን ሥራዎች ይዛዉ እንደተቀመጠችና ለኅብረተሰቡ እንዳላስተዋወቀችዉ ገልፀዋል።

በዘጋቢ ፊልሙ ላይ በቤተክርስቲያኗ ያሉ ምሁራንና በቅዱስ ያሬድ ሕይወትና ሥራዎች ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ አጥኚዎች መሳተፋቸውን በመግለጫው ወቅት ተጠቁሟል።

ከዘጋቢ ፊልሙ የሚገኘዉ ገቢ የደብረሐዌ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳምን ለማሳደስና ለማሰራት እንደሚዉል ኮሚቴዉ አስታዉቋል።ቅዱስ ያሬድ ሚያዚያ 5 ቀን 505 ዓ.ም በአክሱም ከተማ የተወለደ ሲሆን የዜማ ፈጣሪ፣ ባለቅኔ ከመሆኑም ባሻገር የሥነ-ትርጓሜ እዉቀቱ ከፍተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም