ቀጥታ፡

ባለሃብቶች አላስፈላጊ ወጪዎችን በመቀነስ የአገር ኢኮኖሚን ሊደግፉ ይገባል... ምሁራን

አዲስ አበባ ሀምሌ 19/2010 ባለሃብቶች ያላቸውን ሃብት አላስፈላጊ ለሆኑ ወጭዎች ከማዋል ቆጥበው ኢንቨስት ቢያደርጉ በአገሪቱ የሚታየውን የካፒታል እጥረት በመሸፈን የተያዘውን የለውጥ ሂደት ማሳካት ይቻላል ሲሉ ምሁራን ገለፁ። ባለሃብቱ ኢንቨስት እንዲያደርግ የሚያነሳሱ ማበረታቻዎችም በመንግስት በኩል ሊደረጉ እንደሚገባ መክረዋል። ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዶችን ነድፋ በተለይ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ ደፋ  ቀና  እያለች ብትሆንም እቅዶቿን ለማሳካት ማስፈፀሚያ ካፒታል እጥረት እዚህም እዚያም ይስተዋላል። ለዚህም የሚገኘውን ሃብት የመቆጠብ ባህል አለመዳበር አንደኛው ምክንያት ሲሆን ባለሃብቶችም ያገኙትን ሃብት ራሳቸውንና አገርን ለሚጠቅም ስራ ከማዋል ይልቅ ለአላስፈላጊና ጊዜያዊ ወጪዎች በማዋል እንደሚያባክኑም ነው ምሁራኑ የሚገልፁት። በጥረት ሃብት ከሚያከማቹ በተለየ በቀላሉ ሃብትን የሚያገኙ ደግሞ ለማባከን ቅርብ እንደሆኑም ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር አጥላው አለሙና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ያደቴ እንደጠቆሙት በአየር በአየር ስራ ብዙ ሃብት የሚያገኙ ሰዎች ያገኙትን ሀብት በቀላቀሉ ለማጥፋት ተጠቃሽ ናቸው ያሉት ምሁራኑ በልፋት የተገኘ ሀብት ግን በቀላሉ ለማጥፋት ይከብዳል ብለዋል፡፡ በቀላሉ የመጣ ሃብት በቀላሉ ይጠፋል ፤ ምክንያቱም እንደዚያው ይገኛልና ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ለአብነትም በተለይ በመዲናችን ለመዝናናትም ሆነ ለቅንጦት እቃዎች የሚወጡ ወጭዎች የተጋነኑ መሆናቸውን የገለፁት ምሁራኑ ለመዝናናት ዱባይና ሌሎች አገራት ሲኬድ እንደሚታይና በአገር ውስጥም በድሃ አገር የማይደፈር መኪናና የቅንጦት ቤቶች እየተስተዋሉ እንደሆነም ይገልጻሉ። ለታይታው ጫፍ የወጡ ባለሃብቶች የሚያወጡት ወጪ በቀሪው ማህበረሰብ ላይ ጫና የሚፈጥር እንዳይሆንም ግንዛቤ መውሰድ አለባቸው ብለዋል። የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊው አቶ ብርሃኑ በትርፍ፣ በውርስም ሆነ በማንኛውም መንገድ የተገኘውን ገንዘብ ተጨማሪ ገቢ ማመንጨት በሚችል ስራ ማዋል ቢቻል ራስንም ከመጥቀም አልፎ በአገር ኢኮኖሚ ለውጥ ሂደት ላይ የሚታየውን የካፒታል እጥረት በመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚቻልም ገልፀዋል። በተለይ አብዛኛው ወጣት ባለባት አገር ባለሃብቱ ገንዘቡን ለኢንቨስትመንት ቢያውል የስራ አጥነት ጫናውን በመቀነስ አምራች ኃይል ከማውጣት አኳያ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ይሆናል ነው ያሉት። ስራ አጥነትን መቅረፍ ደግሞ ትልቁና በአሁኑ ወቅት አሳሳቢው ተግባር ሲሆን ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈንም ያስችላልም ብለዋል። ብክነትን በመቀነስ የቁጠባ ባህል ሲዳብር እንደ አገር ካፒታል የሚፈልጉ ፕሮጀክቶች ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻልም አሳውቀዋል። ወጪዎቹ ሲወጡ እንኳ በውጪ አገር ከሚወጡ በአገር ውስጥ ቢወጡ ይሻላል ያሉት ዶክተር አጥላው ፤ በአገር ውስጥ ሲወጣ ገንዘቡ እዚሁ አገር ውስጥ የሚቀርና  ይሆናል ብለዋል። በባለሃብቱ የግል ንብረት መንግስት ማዘዝ ባይችልም ሃብታቸውን ወደስራ የመቀየር ተግባር ላይ እንዲሰማሩ መንግስት በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ማበረታቻ ማድረግ እንዳለበት ገልፀዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር አጥላው በበኩላቸው ገንዘባቸውን ለአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት በማዋል ትርፍ የሚያገኙም ሆነ በጎ ተግባር ላይ ለሚያውሉ ባለሃብቶች በስራቸው ውጤት እውቅናና ማበረታቻ የመስጠት ልምድ ሊዳብር ይገባል ብለዋል። በዚህም ባለሃብቱ ገንዘቡን ከማባከን ይልቅ ለስራ እንዲያውለው ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም