ጽህፈት ቤቱ በትምህርት ላይ እያከናወነ ያለው ተግባር ለብልጽግና ጉዟችን ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው -አቶ ርስቱ ይርዳው

ዲላ፤ የካቲት 9/2013(ኢዜአ) የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በትምህርት ላይ እያከናወነ ያለው ተግባር ለብልጽግና ጉዞ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ክልል  ምክትል ርዕሰ መስተዳድር  አቶ ርስቱ ይርዳው ተናገሩ።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ ያስገነባው የባንቆ ዳዳቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመርቋል።

የትምህርት ቤቱ መገንባት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እጦት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሄደው ለመማር የሚገደዱ ታዳጊዎች ችግር እንደሚቀንስ ተገልጿል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት  የተገኙት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንዳሉት ትምህርት ለሀገር ልማት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ተማሪዎች ትኩረታቸውን በትምህርታቸው ሊያደርጉ ይገባል።

በተፈጥሮ ሀብቱና በልምላሜው ውብ የሆነውን የጌዴኦ መልክዓ ምድር በበለጠ ለማልማትና ባለበት እንዲቆይ ለማድረግ እንዲሁም ሳቢነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ትምህርት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

ትምህርት ቤቱ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍና ጉዳት እንዳይደርስበት የአካባቢው ህብረተሰብ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዛሬ በጌዴኦ ዞን ከተመረቀው ሌላ በሸካና ደቡብ ኦሞ ዞኖች በጽህፈት ቤቱ የሚገነቡ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ አመልክተው ይህም የትምህርት ተደራሽነት  ከማሳደግ ባለፈ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን ጠብቀው  እንዲገነቡ ለማድረግ ተነሳሽነትን የሚፈጥር እንደሆነ ገልጸዋል።

በክልሉ ህብረተሰቡን በማስተባበር ቀድሞ የተገነቡ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በክልሉ ለተገነቡ ሶስት ትምህርት ቤቶች አስፈለጊውን ግብዓት በማሟላት ሞዴል ትምህርት ቤቶች እንዲሆኑ ይሰራል ብለዋል።

ትምህርት ቤቱ በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ እንዳስደሰታቸው የገለጹት ደግሞ  የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽፈራው ቦጋለ ናቸው።

የዞኑን የትምህርት ቤት ተደራሽነት እንደሚያሳደግ ተናግረዋል።

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እጦት ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚጓዙ ታዳጊዎች ችግር እንደሚቀንስ አመልክተዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓት የፌደራና ክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን  በትምህርት ቤቱ ውስጥ የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ከዚህ ቀደምም በተለያዩ ክልሎች ያሰገነቧቸው ተመሳሳይ ትምህርት ቤቶች ተመርቀው ለአገልግሎች ዝግጁ መሆናቸውን በወቅቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም